ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ ከሱዳን ጋር ለድርድር የምትቀመጠው ሱዳን መሬቷን ለቃ ስትወጣ ነው -- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

66

የካቲት 16/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ ከሱዳን ጋር ለድርድር የምትቀመጠው በሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት የያዘችውን የኢትዮጵያን መሬት ለቃ ስትወጣ ብቻ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቃ።

ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ማዕቀፍ የሚል የፀና አቋም ስላለን ሌላ አሸማጋይ አንፈልግም ብሏል ሚኒስቴሩ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አምባሳደር ዲና እንዳሉት አገሪቷ በሰሜኑ ክፍል ሕግ በማስከበር ላይ ባለችበት ወቅት ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ ገብታለች።

ሱዳን ከመቶ ዓመት በላይ የቆየውን የድንበር ጉዳይ በሰሜን ኢትዮጵያ ችግር በተፈጠረበት ወቅት እነደ አዲስ ማንሳቷ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት ክንፍ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ መግባት የሁለቱንም አገራት ሕዝብ አይጠቅምም፤ ለቀጣናውም አይበጅም ብለዋል አምባሳደር ዲና።

ኢትዮጵያ እንደ አውሮጳዊያኑ የዘመን ቀመር 1902 በቅኝ ገዥዎች የተሰመረውን ድንበር ተቀብላ በድንበሩ መካከል ያለውን አጠራጣሪ ጉዳይ በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የቆየ ፍላጎት አላት ብለዋል።

በሁለቱ አገራት የተቋቋሙት ሶስት የቴክኒክ የድንበርና የከፍተኛ ኮሜቴዎች ስራቸውን ባልጨረሱበት ወቅት የሱዳን የኢትዮጵያን መሬት መያዝ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ማንም አገር  እናደራድራችሁ ከማለቱ በፊት ችግሩን በሠላማዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎት አላት ያሉት አምባሳደር ዲና ይህ የሚሆነው ግን ሱዳን ከጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም በፊት ወደነበረችበት ስትመለስና የኢትዮጵያን መሬት ለቃ  ስትወጣ ብቻ ነው ብለዋል።

በሱዳን የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማራውን ሃይል መተናኮልም "በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" በመሆኑ የበለጠ ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል አምባሳደር ዲና።

ከዚህ ባለፈም "ኢትዮጵያ ቱርክን አስታርቂኝ ብላ ጠይቃለች" ተብሉ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የሚናፈሰውን ወሬ ሀሰት ብለውታል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያን ጉዳይ በአፍሪካ ማዕቀፍ መፈታት አለበት የሚል ጽኑ አቋም እንዳላት የገለጹት አምባሳደር ዲና ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ሌላ አሸማጋይ አንፈልግም ብለዋል።

ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘም ከመንግሥት በተጨማሪ ከ75 በላይ ዓለም አቀፍ ተቋማት እየሰሩ መሆኑን አምባሳደር ዲና ገልፀዋል፡፡

በዚህም በትግራይ ክልል 36 ወረዳዎች በ92 የዕርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚደረገው ድጋፍ 70 በመቶውን መንግሥት የሚሸፍን ሲሆን ቀሪውን ዓለም አቀፍ ተቋማት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም