ትውልዱ ለአገር አንድነት፣ ዕድገት እና ስላም በመስራት የአድዋን ድል መድገም አለበት--- የፌዴራል ፖሊስ አባላት

76

የካቲት 16/2013 (ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ ለአገር አንድነት፣ ዕድገትና ሉአላዊነት ዘብ በመቆም የአድዋን ድል መድገም ይኖርበታል ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተናገሩ።

የአድዋ ድል ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ ለአፍሪካዊያንና በመላው ዓለም በጭቆና ቀንበር ስር ለነበሩ ጥቁሮች የነጻነት ተምሳሌት ሆኖ የሚታይ ነው።  

ድሉን በማስመልከት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት በፌዴራል ፖሊስ የአሻራና ወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ተፈራ አርጋው የአድዋ ድል የህዝብን አንድነት፣ ነጻነትና የአገር ሉዓላዊነትን በጋራ ማስከበር የተቻለበት መሆኑን ይገልጻሉ።

ድሉ በአራቱም ማዕዘን ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ጥላ ስር ያሰባሰበና የመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት እና መመኪያ መሆኑንም ተናግረዋል።

"ወጣቱ ትውልድ ይህን በመረዳት በዘር፣ በጎሳ እና በሃይማኖት ሳይለያይ አንድነቱንና የአገሩን ሉአላዊነት ማስጠበቅ ይኖርበታል" ብለዋል።

የዘመኑን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ተጠቅሞ የአገሩን ልማት በማፋጠን የአባቶቹን የድል ታሪክ አገርን በማልማት መድገም እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።

አድዋ “ጀግኖች አባቶችና እናቶቻችን ለአገር ሰላምና አንድነት ሲሉ በየጦር ግንባሩ ተዋድቀው ለእኛ ነጻነቷ የተከበረ አገር ያስረከቡበት ነው” ያሉት ደግሞ በወንጀል ምርመራ ቢሮ የኢንተርፖል ኦፕሬሽንና የትራፊክ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ጥሩወርቅ መንግስቴ ናቸው።

ኢንስፔክተር ጥሩወርቅ በተሰማሩበት የሥራ መስክ የህዝብን ሰላም እና ደህንነት በማረጋገጥ የአድዋ ድልን ለመድገም እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

"አሁን ያለነው ትውልድ ለቀጣዩ ታሪክ ከማስተማር ባለፈ የድርሻችንን ሰርተን በተግባር ማሳየት አለብን" ብለዋል።

"ጀግንነት በዘመን ይለካል" ያሉት ደግሞ የብሔራዊ ኢንተርፖል ስልጠና ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር እማኙ አላምረው ናቸው።

"አሁን ያለነው ትውልድ አባቶቻችን ያስረከቡንን ታሪክ ከመጠበቅ ባለፈ በተሰማራንበት የሥራ መስክ የራሳችንን አዲስ ታሪክ መስራት አለብን" ብለዋል

መላው ጥቁር ህዝብ ለነጻነቱ እንዲንቀሳቀስ ምክንያት የሆነው የአድዋ ድል ዘንድሮ 125ኛ ዓመት የሚሞላው ሲሆን በተያዘው የካቲት ወር በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም