በቁልቢ እና ሃዋሳ ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓል በደማቅ ስነ ስርዓት ተከበረ

748

ሐረር ሀዋሳ ሐምሌ 19/2010 በቁልቢ እና ሃዋሳ ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓል ዛሬ በደማቅ ስነ ስርዓትና በሰላም መከበሩን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዲቪዥን ክፍል ኃላፊ  ኮማንደር ስዩም ደገፉ ለኢዜአ እንደገለጹት በሺዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታይዎች በታደሙበት የንግስ በዓል በቁልቢ በሰላም ተከብሯል።

ለዚህም የሀግ አስከባሪዎች  ከምንጊዜውም በላይ ያካሄዱት የወንጀል መከላከል ስራና ህብረተሰቡም ያደረገው ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

በንግስ በዓሉ ላይ ሞባይልና ገንዘብ  ሰርቀው እጅ ከፍንጅ የተያዙ አራት ተጠርጣሪዎችን በገዳሙ አካባቢ የተቋቋመው ጊዜያዊ ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን አስታውቀዋል።

እንዲሁም  ጾታው ወንድ ሆኖ ሳለ የሴት አልባሳት በመልበስ የማታለል ስራ ሲያከናውን የተገኘው አንድ ተጠርጣሪ ደግሞ በምክር መለቀቁን አመልክተዋል።

የስለት ሙክት ሰርቀዋል የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪዎች ማስረጃ አለን በማለታቸው ጉዳያቸው በመደበኛው የሜታ ወረዳ ፍርድ ቤት እንዲታይ መተላለፉም ተጠቅሷል፡፡

ወደ ንግስ በዓሉ ምዕመናኑ መምጣት ከጀመሩበት ካለፈው ሰኞ እስከ ፍጻሜው ድረስ ምንም ዓይነት የትራፊቅ አደጋ አለመድረሱን ጠቁመዋል።

በቁልቢ ገብርኤል ገዳም የተካሄደው የንግስ በዓል ስነ ስርዓት ሲጠናቀቅ ምዕመናኑ ኃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቀው ፈጣሪያቸውን በማመስገን ወደ መጡበት ተመልሰዋል፡፡

በተመሳሳይ በሃዋሳ የተከበረው የቅዱስ ገብርዔል ንግስ በዓል በሰላም መጠናቀቁን የከተማው ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡

በዓሉን ለማክበር ከከተማ እስከ ፌደራል ፖሊስ በቅንጅት መስራታቸውን አመልክተው በዚህም በሰላም መጠናቀቁ አስረድተዋል፡፡

ለበዓሉ በተዘጋጁ ተንቀሳቃሽ ምድብ ችሎቶች አንድ ሞተር ሳይክል ሲሰርቅ እጅ ከፍንጅ የተያዘ ግለሰብ በሶስት ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

ለበዓሉ ስኬታማነት ከህግ አስከባሪዎች በላይ ህብረተሰቡ ላደረገው አስተዋጽኦ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት አመስግነዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ከታደሙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው አቶ ውብሸት አሳምነው በዓሉን ለማክበር ከሻሸመኔ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ውብሸት እንዳሉት ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው በዓሉን ሰላማዊ በሆነ ስነሰርዓት አክብረዋል፡፡

ከአዳማ ከተማ የመጡት ወይዘሮ  አስቴር ያሬድ በበዓሉ በመታደማቸው፣ በህብረተሰቡ አቀባበልና በከተማዋ ሰላም መሆን  መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሳምንት በፊት ዝግጅት ማድረጋቸውንና እንግዶቻቸውን ተቀብለው ማስተናገዳቸውን የተናገሩ ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዋ  ወይዘሮ በሀብቱ አስቻለው ናቸው፡፡