ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ

153

ባህርዳር፣ የካቲት 15 /2013 (ኢዜአ) ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መስጠቱን አስታወቀ።

የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጠው በኬሚስትሪና ታሪክ ትምህርት ክፍሎች መምህርና ተመራማሪ ለሆኑት ዶክተር ማዕረግ አማረና ዶክተር ተመስገን ገበየሁ ናቸው።

በዩኒቨርሲቲው የስትራቴጂክ ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን የድህረ ገጽ ማናጀር ዶክተር ፍስሃ ደርሶ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለምሁራኑ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረጉ የተሰጠው የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ነው።

በዚህም በየስራ ክፍላቸው በምርምር፣ ማስተማር፣ ማህበረሰብ አገልግሎት፣ ፕሮጀክት አስተዳደርና በተለያዩ የአመራር ቦታዎች በማገልገል ባበረከቱት አስተዋጽኦ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መስጠቱን አስታውቀዋል።

"ዶክተር ማዕረግ አማረ በኬሚስትሪ የምርምር መስክ 28 የጥናት ስራዎችን በራሳቸውና ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር ከማሳተማቸውም በላይ ፕሮጀክቶችን በማሸነፍ ሃብት በማመንጨት አስተዋጽኦ አበርክተዋል" ብለዋል።

ዶክተር ተመስገን ገበየሁ በበኩላቸው በታሪክ ዘርፎች ከ15 በላይ የምርምር ስራዎችን በታወቁ ጆርናሎች ማሳተማቸውና የማህበረሰብ አገልግሎት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል።

ምሁራኑ በተለያዩ የስራ ሃላፊነትና የኮሚቴ ስራዎች በመሳተፍም ቀልጣፋ የመማር ማስተማርና የምርምር ተግባራትን በማከናወን ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮውን እንዲወጣ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣታቸው ሴኔቱ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረጉ መስጠቱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም