ነዋሪዎቹ በወንጪ የኢኮ-ቱሪዝም ግንባታ ኑሯቸው እንደሚሻሻል ተስፋ ሰንቀዋል - ኢዜአ አማርኛ
ነዋሪዎቹ በወንጪ የኢኮ-ቱሪዝም ግንባታ ኑሯቸው እንደሚሻሻል ተስፋ ሰንቀዋል

የካቲት 14/2013 (ኢዜአ) በገበታ ለአገር ለሚለማው የወንጪ ፕሮጀክት ለተሳተፉ አካላት የምስጋና መርሃ ግብር በወንጪ ሐይቅ ተካሄዷል።
በምስጋና ስነ ስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ፣ የምዕራብና ደብብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪዎች፣ የወንጪና አካባቢው ነዋሪዎች ታድመዋል።
በገበታ ለአገር ፕሮጀክት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚለማው የወንጪ የኢኮ-ቱሪዝም ግንባታ ሲጠናቀቅ ቱሪስቶችን በመሳብ ለአገሪቷ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጀምርና ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የስራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር ከሚገነባው መሰረተ ልማት ዘላቂ ተጠቃሚ እንደሚሆን የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መገርሳ ድሪብሳ ተናግረዋል።
አካባቢው በተፈጥሮ ኃብት የታደለ በመሆኑ የአካባቢው ማኅብረሰብ በሐይቁ ዙሪያ ያለውን ሀብት መጠበቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
አካባቢው በለውጡ በተሰጠው ትኩረት በመታገዝ እውን የሆነው ፕሮጀክት ከዚህ በፊት ይቀርብ ለነበረው የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል አካባቢውን ከሚጎበኙ ቱሪስቶች ገቢ እያገኙ መቆየታቸውን የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎች ፕሮጀክቱ ካመጣላቸው ፀጋ በመቋደስ ኑሯቸው እንደሚሻሻል ተስፋ ሰንቀዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በተያዘው የገበታ ለአገር ፕሮጀክት ከሚለማው የወንጪ ሐይቅ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም እንዲሁ።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንዲሆን ባላቸው አቅም ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የኦሮሚያ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እስከሚሆን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ሁሉም ዜጋ ፕሮጀክቱ ከግብ እንዲደርስ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
በገበታ ለአገር ከሚለማው የወንጪ ፕሮጀክት በተጨማሪ የክልሉን የቱሪዝም ሃብት የማስተዋወቅና የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የቱሪዝም ኃብት ላይ ብዙ እንዳልተሰራ ጠቁመው ክፍተቱን ለመሙላት ባለኃብቶችን በስፋት ለማሳተፍ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የወንጪ ሐይቅ በገበታ ለአገር ፕሮግራም ከሚለሙት የጎርጎራና ኮይሻ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።
በገበታ ለአገር ፕሮጀክት ኮይሻ፣ ወንጪ እና ጎርጎራን ለማልማት 3 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልፀዋል።