ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር ያላት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ትፈልጋለች…ም/ ጠ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

887

የካቲት 12/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር ያላት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ትፈልጋለች ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ከህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሱብራህማንያም ጄሻንካር ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይተዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል በብዙ ዘርፎች ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት መኖሩን ያደነቁት አቶ ደመቀ፤ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መንግስት ለዜጎቹ እንዲሁም ለስደተኞች የሰብአዊ መብታቸው እንዲጠበቅ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአንድ አንድ ሚዲያዎች የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዳልሆነ ከሚነዛው የሀሰት መረጃ በተቃራኒ ፤ ከመንግሰት በተጨማሪ ከ75 በላይ የአለም አቀፍ ሰብአዊ ዕርዳታ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች አማካኝነት ከ2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ተጠቃሚዎች ዕርዳታ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል 80 % በሚሸፍኑ አካባቢዎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታዎች መሰራጨቱን የገለጹት አቶ ደመቀ፤ ኢትዮጵያ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ከ27 አገራት በመቀበል እያስተናገደች የሚትገኝ ግንባር ቀዳም አገር መሆኗንና መብታቸውም እንዲከበር ተግታ እየሰራች መሆኑዋን አስታውቀዋል።የኢትዮ -ሱዳን የድንበር ውዝግብን ሁለቱም አገሮች ልዩነታቸውን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ዘላቂ መፍትሔ መስጠቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸውም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያና ህንድ መካከል በኢኮኖሚ ዘርፍ የንግድ ልውውጥ እያደገ መምጣቱን በመግለጽ፤ በህንድ ኢንቨስተሮች አማካኝነትም ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩንና በቴክኖሎጂ እና እውቀት ሽግግር እንዲሁም በከፍተኛ አመራሮች ድጋፍ የተሰጠው የባህል ልውውጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም መግባባታቸውንም አስታውቀዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን በመጥቀስ፤ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የህንድ- አፍሪካ ስብሰባ ዝግጅትም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

በውይይቱ መጨረሻም የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ለያዙ አካላት ያለ ቪዛ የመግባት መብት ሰምምነት እንዲሁም የህንዱ ሳይንስና ኢንዳስትሪ ምርምር ም/ቤት እና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባብያ ሰነድ ስምምነት መፈረሙን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።