ምክር ቤቱ ውሳኔዎችን በሳይንሳዊ ጥናት ለመወሰን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር እየሰራ ነው

77

የካቲት 12/2013 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሳይንሳዊ ጥናት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት ከከፍተኛ ትምህርትና ከምርምር ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ምክር ቤቱ የመጀመሪያውን የፓርላማ ምርምር መረብ ጉባኤ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።

አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ምክር ቤቱ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት የሚያከናውናቸው ተግባራት በመረጃ፣ በእውቀትና በተቀመረ ልምድ ላይ እንዲሆኑ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ምርምሮች በማካሄድ ምክር ቤቱ ለጀመረው የለውጥ ስራ በግብዓትነት መጠቀምን ከተግባራቱ መካከል ጠቅሰዋል።

ለዚህም የምርምር ዘርፍ በማቋቋም ከከፍተኛ ትምህርትና ከምርምር ተቋማት፣ ከሲቪልና ከሙያ ማህበራትና ሌሎች ተቋማት ጋር የፓርላማ ምርምር መረብ በመመስረት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የምርምር መረቡ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ለፓርላማ አባላት በማቅረብ በተሟላ መረጃ አስፈጻሚውን ለመጠየቅ ሙያዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።

አፈ ጉባኤው በማኅበራዊ፣ በምጣኔ ሃብትና በፖለቲካ ጉዳዮች የሚደረጉ ክርክሮችና የሚሰጡ ውሳኔዎች ምክንያታዊነት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ጉባኤው ያለውን ፋይዳ አስረድተዋል።

በተሟላ እውቀት ውሳኔ ለመስጠት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ቀጣይት ያለው ጥናትና ምርምር ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው በሳይንሳዊ ጥናት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ባህል እንዲሆን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፓርላማው ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በዛሬው ጉባኤ የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤትና የምርምር መረቡ አባላት በምርምርና ቴክኒክ ስራዎች በጋራ መስራት የሚያስችላቸው የመግባቢያ ሰነድ ቀርቦ ሃሳቦች ተሰጥተዋል።

ጉባኤው በሕግ አወጣጥ ስርዓት፣ በክትትልና ቁጥጥር እና በውክልና ስርዓት ላይ ያተኮሩ 12 ጥናታዊ ፅሁፎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ቀርበው ምክር ቤቱ በሚጠቀምባቸው ሁኔታዎች ላይም መክሯል።

የምክር ቤቱ የፓርላማ ምርምር መረብ ሕዳር 1 ቀን 2012 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት የተካተቱበት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም