የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የመረጃና ደህንነት ተቋማት በመረጃ ልውውጥና በአቅም ግንባታ መስኮች የገቡትን ስምምነት ተግባራዊ እያደረጉ ነው

58

አዲስ አባበ፤ የካቲት 11/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የመረጃና ደህንነት ተቋማት በመረጃ ልውውጥና በአቅም ግንባታ መስኮች የገቡትን ስምምነት ተግባራዊ እያደርጉ መሆኑ ተገለጸ።

የአገራቱ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ቀደም ሲል በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግና በሰው ኃይል የአቅም ግንባታ ዘርፍ ተባብረው ለመሥራት የደረሱትን ስምምነት ተግባራዊ ወደ ማድረግ መሸጋገራቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ተመስገን ጥሩነህ በደቡብ ሱዳን የውስጥ መረጃ ቢሮ ዳይሬክተር ጄኔራል አኮል ኮር ኩክ የተመራውን የደቡብ ሱዳን የመረጃና ደህንነት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአገሪቱ ከፍተኛ የፀጥታ አካላት ልዑካን ቡድን ተቀብለው በሁለትዮሽና ቀጣናዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

የሁለቱ አገራት የመረጃና ደህንነት ኃላፊዎች ከሶስት ሳምንታት በፊት በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ ለመለዋወጥ፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ እንዲሁም አካባቢያዊ ስጋቶችን ለማስወገድ የደረሱትን ስምምነትም በተመለከተ ምክክር አድርገዋል ።

የመረጃና የደህንነት ተቋማቱ ህገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሣሪያ ዝውውሮችን ጨምሮ ሽብርተኝነትንና በድንበር አካባቢ የሚታዩ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ቀጣናዊ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ በኩል ውጤታማ ሥራዎች ማከናወናቸው ተገልጿል።

በቀጣይ አገራቱ ስትራቴጂክ አጋርነታቸውን በማጠናከር በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በመረጃና ደህንነት ዘርፎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ተመላክቷል።

ከውይይቱም በኋላ የደቡብ ሱዳን የውስጥ መረጃ ቢሮ ዳይሬክተር ጄኔራል አኮል ኮር ኩክ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘውን የብሄራዊ መረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ጎብኝተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በኢንስቲትዩት ደረጃ በነበረበት በ1977 ዓ.ም በመረጃ ዘርፍ ሥልጠና መውሰዳቸውን የገለፁት ጄኔራል አኮል ኮር ኩክ፤ አሁን በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደረጃ በማደጉ ልዩ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በመረጃና ደህንነት የጥናትና ሥልጠና ዘርፎች በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል የመሆን አቅም ያለው በመሆኑ በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ለደቡብ ሱዳን የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጄኔራል አኮል ኮር ኩክ ተናግረዋል፡፡

አገራቸው የመረጃ ኦፊሰሮችን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የማሰልጠን ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ወዳጅነት የመሠረቱ ከመሆናቸውም በላይ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ነጻ እንድትወጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡

ደቡብ ሱዳን ነፃነት ካገኘች በኋላም ባጋጠማት የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷ አይዘነጋም፡፡

በዚህም አገራቸው ውለታዋን እንደማትረሳ ጄኔራል አኮል ኮር ኩክ መግለፃቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም