የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ በመቋረጡ ተቸግራናል ፡- የግራር ጃርሶና ደብረ ሊባኖስ ወረዳ ነዋሪዎች

71
ፍቼ  ሀምሌ 19/2010 የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ በመቋረጡ ምክንያት መቸገራቸውን በሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶና ደብረ ሊባኖስ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገለጹ። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፍቼ ዲስትሪክት በበኩሉ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት የሰጡ የኤሌክትሪክ መስመሮች በእርጅና ምክንያትና በኃይል አጠቃቀም ጫና ምክንያት እየተበጣጠሱ ችግሩ መከሰቱን ተናግረዋል። ነዋሪዎቹና አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ለአዜአ እንዳሉት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ  በሥራቸው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው ነው። በተለይ ጠፍቶ ሲበራ በሚፈጠረው የኃይል መዋዠቅ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እየተቃጠሉባቸው ለጉዳት መዳረጋቸውን ገልጸዋል። ከቅሬታ ቅራቢዎቹ መካከል በደብረ ሊባኖስ ወረዳ በህክምና ሙያ የሚተዳደሩት አቶ በላይ ፈጠነ በበኩላቸው የኃይል መቆራረጥ ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ህክምና ፍለጋ ወደ ጤና ተቋማቸው ለሚመጡ ሕሙማን የላቦራቶሪና የኤክስሬይ ምርመራ አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን አስረድተዋል። ይህም ስራቸውን ከማስተጋጎሉ በላይ ገቢያቸውን እየጎዳው በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል። በግራር ጃርሶ ወረዳ የወርጡ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አደነች መኮንን በበኩላቸው የመብራት ችግር በመባባሱ ለሻማ የሚያወጡት ወጪ ከፍ እያለ መምጣቱን ተናግረዋል። እሳቸው እንደሚሉት በየወሩ ያልተጠቀሙበትን የኤሌክትሪክ ሒሳብ ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጉ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል። በአሁኑ ወቅትም በአካባቢያቸው መብራት ከጠፋ ከአንድ ሳምንት በላይ በማስቆጠሩ መማረራቸውን ነው የገለጹት። በኦሮሚያ ብድር ቁጠባና እገዝ ተቋም የግራር ጃርሶ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁንዴ ኦላና በበኩላቸው እንዳሉት ለተቋማቸው የእለት ተእለት ሥራ የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ ቢሆንም በተዳጋጋሚ ሰለሚቆራረጥ ደንበኞችን በአግባቡ ለማስተናገድ ተቸግረዋል። ከችግሩ ስፋትና አንገብጋቢነት አንጻር የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ  ፈጠን  መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት እለታዊ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዳዳገታቸው የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፍቼ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ፍቅሬ ናቸው። ድርጅቱ በጀነሬተር የመጠቀም ልምድ ቢኖረውም የመብራት መጥፋት ከሌሎች መሰል መስሪያ ቤቶች ጋር ባለው ግንኙነት ላይ የራሱን ችግር እየፈጠረበትና ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረገ መሆኑን አመልክተዋል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፍቼ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲሳ ጫላ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ችግሩ በሁለቱ ወረዳዎችና አጎራባች በሆኑ 17 የገጠር ቀበሌዎች መኖሩን አምነዋል። " የኃይል መቆራረጥ እየተከሰተ ያለው ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ የኤሌትሪክ ገመዶችና ትራንስፎርመሮች በማርጀታቸው እንዲሁም በዝናብ ፣ በመብረቅና በንፋስ ጉዳት ሲደርስባቸው በቃላሉ የሚበጣጠሱ በመሆኑ ነው" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ችግሩን በዘላቂነት ለማቃለል 120 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ዘመናዊ አዲስ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና ተጨማሪ ሰብስቲቱዩሽን የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ በአካባቢው ለመትከል ከዋናው መስሪያ ቤት ጋር በመሆን አየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት በሰው ኃይልና በማንዋል መሳሪያ በመታገዝ የተቃጠሉ የኃይል ማስተላለፊያዎችን በማፈላለግ ለመጠገን  ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። አንዳንድ ደንበኞች ከሒሳብ ክፍያ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ካላቸው በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት ምርመራ ተካሂዶ የተጠቀሙበትን ሒሳብ ብቻ እንዲከፍሉ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል። በኃይል መዋዠቅ ምክንያት የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች የተቃጠሉባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ካሉ የሚጠየቁትን ህጋዊ ማስረጃ በወቅቱ ካቀረቡ ተቋማቸው ግምቱን የሚከፍልበት የአሰራር ሥርዓት እንዳለውና በዚህም መጠቀም እንደሚችሉ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም