ኢትዮጵያ የድንበር ውዝግቡን ለመፍታት የተከተለችው ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ለዘላቂ ሠላም እንደሚበጅ ምሁራን ገለጹ

872

ጎንደር ፤ የካቲት 10/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የሱዳንን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት የተከተለችው ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ለቀጠናው ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንደሚበጅ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡

በዩኒቨርሲቲው በተካሄደው የኢትዮ ሱዳን ታሪካዊ ግንኙነት ኮንፍረንስ ላይ ምሁራኑ እንደተናገሩት የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ለማስቀጠል አለመግባባቶችን በሰለጠነና በሰከነ መንገድ በውይይት መፍታት አማራጭ የለውም፡፡

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ምሁር  ፕሮፌሰር ኢብራሂም ዳምጠው ሱዳን በድንበር ሽፋን የሶስተኛ ወገን የጦርነት ተልእኮ ተቀብላ ለማራመድ  የመረጠችው አካሄድ ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የቅኝ ገዢዎችን ቅስም የሰበረች ነጻ አፍሪካዊ ሀገር እንደመሆኑዋ እድገቷንና ልማቷን በማደናቀፍ የተዳከመች ሀገር ለማድረግ በውስጥም ሆነ በውጪ በርካታ ሴራዎች ሲፈጸሙባት መቆየቱን አውሰተዋል።

የሱዳንና ኢትዮጵያ መልካም ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በኢትዮጵያ በኩል የሚደረገውን ሠላማዊ ጥረት ሱዳን በተመሳሳይ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ለቀጠናው መረጋጋት የበኩሏን ጥረት ልታደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት በቀደመ ታሪካቸው በማንኛውም ወቅት ግጭት ውስጥ ሳይገቡ በመልካም  ጉርብትና የተጠናከረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መስርተው የቆዩ ወዳጅ ሀገራት ናቸው  ያሉት በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ምሁር ዶክተር  ቡሻ ተኣ  ናቸው፡፡

ሱዳን በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ወቅት ሻለቃ ግዮን በተባለ ግለሰብ ኢትዮጵያን ባላሳተፈ መንገድ ድንበር የመከለል ተግባር ተከናውኖ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት  እንደሚያመለክቱ ጠቅሰዋል፡፡

የድንበር ውዝግቡ ከሱዳን ህዝብ እይታና ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማዳከም በሚፈልግ በሶስተኛ ወገን ግፊት የሚከናወን የውክልና ጠብ አጫሪነት ተግባር ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን ለመፍታት የጀመራቸው ሠላማዊ ጥረቶች የሚደገፉ ናቸው ያሉት ዶክተር ቡሻ የሁለቱ ሀገራት ምሁራን ውዝግቡን ለመፍታት የሚያስችሉ ታሪካዊ መረጃዎችን በማደራጀት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ምክትል ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ጋሻው አንዳርጌ በበኩላቸው መንግስት ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ውዝግቦቹን በሰከነ እና የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መንገድ ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የድንበር አካባቢዎች ታሪካዊ ዳራዎች ግምት ባስገባና የተሻለ እውቀት ያላቸውን ምሁራን ፣ፖለቲከኞችና ዲፕሎማቶችን በማሳተፍ ለድንበሩ መካለል ዘላቂ እልባት መስጠት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ከሱዳን አቻው ጋር የጀመረውን ግንኙነት አጠናክሮ በመቀጠል የድንበር ውዝግቡ የሁለቱን ሀገራት የቆየ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማስቀጠል በሚያስችል መልኩ እንዲፈታ በጋራ ለመስራት መዘጋጀቱም ተመልክቷል፡፡

በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር በተዘጋጀው የአንድ ቀን ኮንፍረንስ  የሱዳንና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች የታሪክ የቅርስና የማህበረሰብ ሳይንስ ምሁራን  ተሳትፈዋል፡፡    

በኮንፍረንሱ የተገኙት የሱዳን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና አርት ምሁር ዶክተር ኦማር አልአሚን ሱዳንና ኢትዮጵያ ዘመናት የዘለቀውን የጋራ ግንኙነታቸውን መሰረት በማድረግ የድንበር አለመግባባቶቻቸውን በውይይትና ስምምነት ሊፈቱ እንደሚገባ በማብራራት መናገራቸውን ኢዜአ ትናንት ዘግቧል፡፡