በአዲስ አበባ አሮጌ ላዳ ታክሲዎችን በዘመናዊ ታክሲዎች ለመተካት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል 6 ቢሊዮን ብር ብድር ተዘጋጅቷል

128

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10/2013 ( ኢዜአ)  በአዲስ አበባ አሮጌ ላዳ ታክሲዎችን በዘመናዊ ታክሲዎች ለመተካት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል 6 ቢሊዮን ብር ብድር መዘጋጀቱ ተገለጸ።

ላዳ ታክሲዎችን በዘመናዊ ታክሲዎች ለመተካት የሚያስችል ስምምነት በአዲስ አበባ ላዳ ታክሲዎች ማህበራት እና ኤላ አውቶ ኢንጂነሪግ ኩባንያ መካከል ተፈርሟል።

በማህበራቱ በኩል የማህበራቱ ሰብሳቢ አቶ ቢንያም መለሰ ሲፈርሙ በኩባንያው በኩል ደግሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ በቀለ አበበ ፈርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት ኩባንያው ዘመናዊ ታክሲዎችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም አሮጌ ላዳዎችን በአዲስ የመተካት ስራ ይሰራል።

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል 6 ቢሊዮን ብር ብድር መዘጋጀቱም በስምምነቱ ላይ ተገልጿል።

20 በመቶ ክፍያ ሲፈጽሙ 80 በመቶውን ንግድ ባንክ የሚሸፍን መሆኑም ተመልክቷል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ስጦታው አካለ እንደተናገሩት፤ የስምምነቱ ዓላማ ለከተማው ነዋሪ ቀልጣፋ እና ምቹ የትራንስፖት አገልግሎት ለመስጠት ነው።

አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ላዳ ታክሲዎች እስከ 50 ዓመት ያለፋቸው መኖራቸውን ጠቅሰው ይህም ባለንብረቶችም ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኙ ማድረጉን አንስተዋል።

ኢንጂነሩ እንዳሉት፤ በቀጣይ የሚቀርቡ ዘመናዊ ታክሲዎች የባለንብረቶችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ገበያ እንዲያገኙ ያደርጋል።

ኤላ ኢንጂነሪንግ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ታክሲዎችን እየገጣጠመ ያቀርባል።

የአዲስ አበባ ላዳ ታክሲዎች ማህበራት ከ10 ሺህ በላይ አባላት የያዘ ሲሆን 185 ማህበራትን ያካተተ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም