ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የማህበረሰቡን ችግር በዘላቂነት እንዲፈቱ መስራት እንዳለባቸው ተመለከተ

1804

መቱ፣ የካቲት 09/2013(ኢዜአ)፡- ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ግኝቶች የየአካባቢው ማህበረሰብን ችግር በዘላቂነት እንዲፈቱ  መስራት እንዳለባቸው ተመለከተ።

“የማህበረሰብን ችግር ለመፍታት የጥናትና ምርምር አዳዲስ ግኝቶች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ  አምስተኛው ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በመቱ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።

 በጉባኤው የተጋበዙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ኢንጂነር ፍሰሐ በሁሉ እንደገለጹት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎችን በመደገፍ የኢንዱስትሪ ትስስርን አጠናክረው  ማህበረሰብ አቀፍ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማካሄድ ለሀገሪቱ እድገት ከፍተኛ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል።

ሳይንስና ቴክኖሎጂን በመጠቀምም የኢኮኖሚ ዕድገትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማምጣት ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሱልጣን ሱሌማን በበኩላቸው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረቱ የጥናትና ምርምር ስራዎች ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈቱ ለማስቻል ለማህበረሰቡ ማመቻቸትና  ማሳተፍ  እንዳለባቸው አመልክተዋል።

“በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተሠሩት የጥናትና ምርምር ስራዎች  ላይ የዋሉት ጥቂቶች ናቸው” ያሉት ደግሞ የጉባኤው ተሳታፊ  ረዳት ፕሮፌሰር ብዙአየሁ ደገፈ ናቸው።

አጥኚዎችና ፖሊሲ አርቃቂዎች ማህበረሰብን ማዕከል ያደረጉ ምርምሮች ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የጥናትና ምርምር ስራዎችን ወደ ሀገሪቱ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ስራ ላይ በማዋል  የማህበረሰቡ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ለማስቻል ምሁራንና ባለድርሻ አካላት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ተወካይ ዶክተር በደሉ ተካ እንደተናገሩት ተቋሙ  በጥናትና ምርምር የአካባቢውን  ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ።

 “ዓለምን ለሚፈታተኗት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫ ከማሳየት አኳያ ዩኒቨርሲቲዎች የአንድ ሀገር ወሳኝ ተቋማት ናቸው ያሉት ደግሞ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር እንደገና አበበ ናቸው።

በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም አዳዲስ የምርምር ግኝቶችን በመጠቀም ለማህበረሰቡ ዕድገት መስራት አለብን ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ጉባኤው የመቱ፣ ጅማ፣ አምቦ፣ ወለጋ፣ ጋምቤላና የሚዛን ቴፒ  ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን  ተሳትፈዋል።