ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ ያሉ የጉምሩክ ፍተሻ ጣቢያዎች የሚስተዋለው ብልሹ አሰራር ለስራቸው እንቅፋት እየፈጠረባቸው ነው ፡- አሽከርካሪዎች ።

63
ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ ባሉ የጉምሩክ ፍተሻ ጣቢያዎች ላይ የሚስተዋለው ብልሹ አሰራር በስራቸው ላይ እንቅፋት እየፈጠረባቸው መሆኑን በደረቅ ጭነት ማመላለስ ተግባር ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪዎች ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በበኩሉ ችግሩ የተፈጠረው በፍተሻ ጣቢያዎች ላይ እየተደረገ ባለው ማሻሻያ ምክንያት መሆኑን ጠቁሟል። ከጂቡቲ አዲስ አበባ በደረቅ ጭነት ማመላለስ ተግባር የተሰማሩ አሽከርካሪዎች ለኢዜአ ባቀረቡት ቅሬታ እንደገለጹት፤ በጋላፊ፣ሚሌ፣ አዋሽና አዳማ የጉምሩክ የፍተሻ ጣቢያዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ወረፋ በመኖሩ ለእንግልት ተዳርገዋል። በየጣቢያው መጉላላት የሚፈጠርበት ምክንያት የሚመደቡ ሰራተኞች ስራቸውን በአግባቡ ባለመስራታቸውና የስራ ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ እንደሆነ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል። በተለይም በጋላፊ ፍተሻ ጣቢያ መኪናዎች እስከ 20 ኪሎሜትር የሚደርስ ርቀት ተደርድረው እንደሚቆሙና አንድ ቀን ሙሉ እንደሚቆዩ ገልጸዋል። ቅሬታቸውን ካቀረቡ አሽከርካሪዎች  መካከል በላይ መለሰ እንደሚለው በየኬላዎች በመጀመሪያ ያለ ችግር ምንድን ነው ሰዎች በፍላጎት አይደለም የሚሰሩት ብለዋል፡፡ ይልማ ደምሴ በበኩሉ “የጉምሩክ ሰራተኞች አሉ ከእኛ በላይ ነው ከአዲስ አበባ የመጣ መመሪያ ነው ይሉሃል፤አዲስ አበባ አይደለም አንተ እዛ ያለውን አለቃ እንኳን ለማናገር ጊዜ የለህም፡፡  የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን በበኩላቸው አሽከርካሪዎች ቅሬታ ማቅረባቸውንና ባለስልጣኑም ችግሩ ስለመኖሩ እንደሚያውቅ አረጋግጠዋል። ችግሩ የተፈጠረው በቅርብ በኬላዎች አካባቢ እየተደረገ ባለው እድሳት ምክንያት ፍተሻ የሚደረገው መስመር ላይ እንደሆነም ገልጸዋል።  በተጨማሪም ከጂቡቲ የተለያዩ እቃዎችን የጫኑ በርካታ መኪኖች በአንድ ጊዜ ተከታትለው መግባት ለችግሩ መፈጠር አስተዋዕኦ እንደነበራቸው ተናግረዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ሰራተኞች ሙሉ ጊዜ እንዲሰሩ በማድረግና ከሲስተም መቆራረጥ ጋር ያለውን ችግርም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመነጋገር እንዲስተካከል መደረጉን ገልጸዋል። በሰራተኞች በኩል የተነሳው የስነምግባር ችግር በባለስልጣኑ ትኩረት የሚደረግበት በመሆኑ በማንኛውም መንገድ ደንበኛ የሚያጉላሉ ሰራተኞች ካሉ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።  አልፎ አልፎ በየጣቢያዎች ላይ በሚያጋጥሙ ጊዜያዊ ችግሮች ላይ አሽከርካሪዎች ችግሩን በመረዳት በትዕግስት የመጠበቅ ልምድ ሊኖር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በተጨማሪም በምንም አይነት መንገድ ተገልጋይ የሚያጉላሉ ሰራተኞች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ ለመስሪያ ቤቱ ጥቆማ መስጠት እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም