የአማራ ክልል ዓመታዊ የባህል ስፖርቶች ውድድር በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አሸናፊነት ተጠናቀቀ

57

ደሴ ፤ የካቲት 8/2013 (ኢዜአ)  በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአማራ ክልል ዓመታዊ የባህል ስፖርቶች ውድድር በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አጠቃላይ አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቀቀ።

በድሬደዋ ከተማ ለሚካሄደው የባህል ስፖርቶች ውድድር ክልሉን የሚወክሉ  ስፖርተኞች ተመርጠዋል።

በክልሉ ስፖርት ኮሚሽን የማህበራት ማደራጃ  ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ሉሌ እንደገለጹት ጥር 30 / 2013 ዓ/ም ሲካሄድ በቆየው የባህል ስፖርት ውድድር 14 ዞኖች ተሳትፈዋል፡፡፡

ገና፣  ገበጣ፣ ትግል፣ ፈረስ ጉግስን ጨምሮ በአስር ዓይነት የባህል ስፖርት ውድድሮች  633 ስፖርተኞች መከፈላቸውን አስረድተዋል።

በውድድሩም ጠንካራ ዝግጅት ያደረገው የአዊ ብሔረሰብ አስዳደር ዞን 36 ነጥብ በማምጣት አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን ደቡብ ጎንደር በ33 ነጥብ ሁለተኛ፣  ደቡብ ወሎ ደግሞ 32 ነጥብ በማምጣት ሦስተኛ ሆነው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በድሬደዋ ከተማ ለሚካሄደው ተመሳሳይ ውድድር ክልሉን የሚወክሉ 53  ስፖርተኞች ተመርጠዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ቃልአብ ካህሊ በበኩላቸው ባደረጉት ጠንካራ ቅደመ ዝግጅት አንደኛ መውጣታቸው ጠቁመው፤  በየጊዜው የሚካሄደው ዓመታዊ ስፖርቶች አንድነታችንንና አብሮነታችን ለማጎልበት  አግዞናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርት ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ኃይሌ ቀጣይ በድሬደዋ ከተማ ለሚካሄደው 18ኛ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርትና 14ኛ የባህል ፌስቲቫል ውድድር  ዝግጅት መጠናቀቁን አስታወቀዋል።

ከየካቲት 21 እስከ 27/2013 ዓ.ም. ለሚካሄደው ዓመታዊ የስፖርት ውድድሮችና ፌስቲቫልም ክልልች ስፖርተኞችን በመምረጥ እንዳዘጋጁ አመልክተው  በ11 የስፖርት ዓይነቶች ከ800 በላይ ስፖርተኞች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

ባህላዊ የስፖርት ውድድሮች የስፖርት ቱሪዝሙን ከማጎልበታቸውም ባለፈ እየተሸረሸረ የመጣውን የአንድነትና  አብሮነት እሴት ለማጠናከርም አይነተኛ ሚና አለው ብለዋል።

ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የመጣው ወጣት ስጦታው ጌታወይ በሰጠው አስተያየተ በውድድሩ ባሳየው እንቅስቃሴ መመረጡንና  ክልሉ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ  ከወዲሁ እንደመዘጋጅ ገልጿል" ገልጿል፡፡

በማጠናቀቂያ ሥነ-ሥርዓት  የስፖርት ቤተሰቦች፣ ከፌደራል፣ ክልሉና ዞኑ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም