የመካከለኛ ደረጃ የግብርና ባለሙያዎችን የማፍራት ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል-ኮሌጁ

53

ጎባ የካቲት 8/2013  (ኢዜአ) አርሶና አርብቶ አደሩን በእውቀትና በክህሎት የሚደግፉ የመካከለኛ ደረጃ የግብርና ባለሙያዎችን የማፍራት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የአጋርፋ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ አስታወቀ።

 ኮሌጁ ለ17ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች በደረጃ አራት ያሰለጠናቸውን 467 ተማሪዎች ትላንት አስመርቋል።

ኮሌጁ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በእጽዋትና እንስሳት ሳይንስ፣ በአነስተኛ መስኖና በተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ የተሰጣቸውን ሰልጠና በአግባቡ ያጠናቀቁ መሆናቸው ተመልክቷል።

የኮሌጅ ዲን ዶክተር ጫላ ፈዬራ በወቅቱ እንደገለጹት መንግስት አርሶና አርብቶ አደሩን ከልማዳዊ የአስተራራስ ዘዴ በማላቀቅ ዘመናዊና ገበያ ተኮር ግብርና እንዲከተል እያደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡ 

"አርሶ አደሩ ከእጅ ወደ አፍ ከነበረው የግብርና እሳቤ ገበያን ማዕከል በማድረግ ማምረት መጀመሩ የጥረቱ አካል ነው" ብለዋል፡፡ 

ዶክተር ጫላ እንዳሉት መንግስት አርሶና አርብቶ አደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆንና ዘመናዊ እርሻን እንዲከተል በእውቀትና በክህሎት የሚደግፉ በመካከለኛ የሙያ ደረጃ ላይ የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ይገኘል፡፡ 

ሰልጣኞች የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በመረዳት በኮሌጁ ቆይታቸው በንድፈ ሀሳብና በተግባር የቀሰሙትን እውቀት ለማህበረሰብ ለውጥ እንዲያውሉ አስገንዘበዋል፡፡

የፌዴራል ግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ቦርድ ሰብሳቢ ተወካይ ወይዘሪት ኤልዲያና ሱሌይማ በበኩላቸው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣትና የግብርናው መስክ በሀገር ኢኮኖሚ የመሪነት ሚናውን በብቃት እንዲወጣ በዘርፍ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

መንግስት በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች ግብርናን በማዘመን አርሶና አርብቶ አደሩን በእውቀት ለመደገፍ የግብርና ቴክኒክና ኮሌጆችን ከፍቶ  እየሰራ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

ተመራቂዎች በኮሌጁ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተጠቃሚነት ተግተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ከተመራቂዎች መካከል ጋሻው እንደሻው በኮሌጁ ቆይታው የገበየውን እውቀት ለማህበረሰብ ለውጥ ለማዋል መዘጋጀቱን ተናግሯል።

''አርሶና አርብቶ አደሩ በአካባው የሚገኙ የተለያዩ የውኃ አመራጮችን በመጠቀም በመስኖ ልማት እንዲሳተፍ በተማርኩርት የመስኖ ምህድስና ዘርፍ ህዝቡን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነኝ ''ያለው ደግሞ  ተመራቂ አቤል ግርማ ነው፡፡ 

በ1975 ዓ.ም የተቋቋመው የአጋርፋ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ የትላንቶቹን ጨምሮ ከ21ሺህ የሚበልጡ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም