በአዲስ አበባ የመረጃ ማመልከቻ ቋት ማዕከል ሊገነባ ነው

130

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7/2013 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የመረጃ ማመልከቻ ቋት ማዕከል በ49 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ሊያስገነባ መሆኑ ተገለጸ።

ግንባታው እስከ ሰኔ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ ነጫ ገልጸዋል።

ወሳኝ ኩነት በሚሰጥባቸው ዘርፎች በርካታ እሮሮዎች እንዳሉ ጠቁመው ይህንን ችግር ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠት አሰራሩን ያዘምነዋል ብለዋል።

የአሰራሩ መዘመን ብልሹ ተግባራትን በመቅረፍ ረገድም ትልቅ ሚና አለው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ቋቱ ተግባራዊ ሲደረግ የሲስተም መቆራረጥ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ ደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

ተቋሙ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ ያሉ ፋይሎችን ወደ ሶፍት ኮፒ የመገልበጥ ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡

በዚህም የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን በማቀላጠፍ ደንበኞች መረጃ ፈልገው ሲመጡ እንዳይጉላሉ የማዕከሉ ግንባታ ጉልህ ሚናን ይጫወታል ነው ያሉት ዶክተር ታከለ።

ተቋሙ የመታወቂያ አሰጣጥ ሂደቱን ዲጂታላይዝ ማድረግ ከመጀመሩ በፊት ከሚሰጠው የመታወቂያ ቁጥር በእጥፍ መስጠት እንዲችል ማድረጉንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም