በሐዋሳ በከተማ ግብርና ልማት የተሰማሩ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ

116

ሐዋሳ፣  የካቲት 7/2013(ኢዜአ) በከተማ ግብርና ስራ ላይ ተሰማርተው አትክልት በማልማት ከራሳቸው ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አንዳንድ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የከተማ ግብርና ውጤታማ እንዲሆን የዘር አቅርቦትና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

በሐዋሳ ከተማ የሐዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አርሶ አደር አየለች አዋቶ በሰጡት አስተያየት በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ቲማቲም፣ሽንኩርት፣ጥቅል ጎመንና ቃሪያ በመስኖ በማልማት ውጤታማ ሆነዋል።

በአነስተኛ መሬት ላይ በጀመሩት የከተማ ግብርና ውጤት በማየታቸው አሁን ላይ የጉድጓድ ውሃን በጀነሬተር በመሳብ በዓመት ሶስት ጊዜ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከመስኖ ልማት እንቅስቃሴውም በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገቢ በማግኘት ኑሯቸውን ለማሻሻል መቻላቸውን ገልፀዋል።

የልማቱ ስራ አዋጪ በመሆኑም ለ35 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ማመቻቸታቸውን አብራርተዋል።

የገበያ እድል ባለመመቻቸቱ ምርታቸውን በቀጥታ ለገበያ ማቅረብ ባለመቻላቸው በደላላ ጣልቃ ገብነት የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ መሆኑ እንዳልቻሉም ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ አጠና ተራ ኮንዶሚኒየም ነዋሪ ወይዘሮ ብርቱካን ገብረሚካኤል በበኩላቸው የወዳደቁ የዘይትና ሃይላድ ዕቃዎችን ጭምር ተጠቅመው በጓሮዋቸው ቆስጣ፣ቃሪያና ሌሎችንም አትክልቶች በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ከማህበራዊ ድህረ-ገፅ ባገኙት መረጃ ተነሳስተው ልማት ውስጥ በመግባት ለቤተሰብ ፍጆታ የሚሆን በማምረት ለአስቤዛ ያወጡ የነበረውን ወጪ ከማዳን ባለፈ ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምርቶችን በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የሀዋሳ ከተማ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበባየሁ ላለማው በዘንድሮው በጋ የመስኖ ልማት ከ24 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በመሳተፍ አንድ ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የከተማ ግብርና ልማት ውጤታማ እንዲሆንም መምሪያው የዘር አቅርቦትና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በከተማዋ እየተካሄደ ካለው ከዚሁ ልማት እንቅስቃሴ 385 ሺህ ኩንታል የተለያዩ አትክልቶችን ለማምረት መታቀዱን ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ግብርና ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ሻሾ በመጀመሪያውና በሁለተኛ ዙር እየተካሄደ ባለው የመስኖ እርሻ ከ54 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል።

ከዚህ ውስጥ በሐዋሳ ከተማ እየተከናወነ ያለው የመሬትና ከመሬት በላይ የመስኖ እርሻ በመልካም ሁኔታ እንደሚገኝ ጠቅሰው በተለይ ከመሬት በላይ የተጀመረው የጓሮ አትክልት ልምድን በመቀመር ለማስፋፋት እየተሰራ ይገኛል።

“ቀደም ሲል በምርጥ ዘር አቅርቦት ረገድ የነበረውን ቅሬታ ለመፍታት ከአቅራቢ ድርጅቶች ጋር በተፈጠረው ቅንጅት ከ640 ኩንታል በላይ ግብዓት ተሰራጭቷል” ብለዋል።

ከገበያ ጋር በተያያዘ የተነሳው ቅሬታ ተገቢ መሆኑን አምነው “ችግሩን ለመፍታት ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን አሠራር ለመዘርጋት ይሰራል” ብለዋል።

በተለይ ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎችና መሰል ተቋማት ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በክልሉ ከበጋ መስኖ ልማቱ ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም