ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የአትሌቲክስ ስፖርት አካዳሚ ሊከፍት ነው

76

ጎንደር፣ የካቲት 7/2013 ( ኢዜአ)  የደባርቅ ዩንቨርሲቲ በአትሌቲክስ ስፖርት የሰለጠነ የሰው ሃይል በብዛትና በጥራት ለማፍራት የሚያስችል የአትሌቲክስ ስፖርት አካዳሚ ለመክፈትእየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አበጀ ታፈረ ለኢዜአ እንደተናገሩት አካዳሚውን ለመክፈት የታሰበው የሰሜን ተራሮች መልክዓ ምድርና የአየር ንብረት ለዘርፉ ልማት ለማዋል ነው።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት የምትታወቅበትን የአትሌቲክስ ስፖርትን በሳይንሳዊ መንገድ በመምራት ታዋቂ አትሌቶችን ለማፍራት የሰለጠነ የሰው ሃይል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ ዓመት ለመክፈት ካቀዳቸው አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች መካከል የአትሌቲክስ ስፖርት እንዲሆን ተወስኖ ወደ ስራ መገባቱን አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የአካዳሚውን አስፈላጊነት በተመለከተ ምክክር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ጠቃሚ ግብአቶችን የማሰባሰብና የማደራጀት ተግባራት ተከናውኗል ብለዋል።


የአትሌቲክስ ስፖርት አካዳሚው የሚመራባቸው የአሰራርና የአደረጃጀት መዋቅሮች እየተጠኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የስርአተ ትምህርት ቀረጻና ዝግጅት በቅርቡ እንደሚጀመርም ተናግረዋል። 

አካዳሚው በአትሌቲክስ ስፖርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያሰለጥን ሲሆን ደረጃ በደረጃም በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ የሚያሰለጥን መሆኑን ተናግረዋል። 

"ደባርቅና አካባቢው ታዋቂ አትሌቶች መፍለቂያ ቦታ ነው" ያሉት የሰሜን ጎንደር ስፖርት መምሪያ የስፖርት ማህበራት ማደራጃ፤ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ስልጠናና ውድድር ቡድን መሪ አቶ አየልኝ ካሳ ናቸው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ በትላልቅ ክለቦች የታቀፉ ከ80 በላይ አትሌቶች ከደባርቅና አካባቢው የፈለቁ መሆናቸውን በማሳያነት አቅርበው የአካዳሚው መከፈት ዘርፉን በእውቀት በመምራት ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ነው ያሉት።

ከነዚህ ውስጥም በቶኪዮ ኦሎምፒክ እንዲሳተፉ ከተመለመሉ ስፖርተኞች መካከል 3ቱ ከደባርቅና አካባቢው መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

በደባርቅና በዳባት ከተሞች ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ የአትሌቲክስ መንደሮች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው የሚከፍተው አካዳሚ ለአትሌቲክስ መንደሮቹ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።

በ2010 ዓ.ም ወደ ስራ የገባው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በ23 የትምህርት መስኮች 3 ሺ 858 ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም