በጃፓን የተከሰተው ርዕደ መሬት ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት አስከተለ

994

የካቲት 07/2013 (ኢዜአ) በሰሜናዊ ምስራቅ ጃፓን የተከሰተው ርዕደ መሬት ከፍተኛ የሆነ የመሬት መንሸራተት አስከትሏል።

ይህ ሪፖርት እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የሞተ ሰው ስለመኖሩ ያልተገለጸ ሲሆን በአደጋው ግን ከ140 በላይ ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ቲ አር ቲ ዘግቧል።

አደጋው ከተከሰተ በኋላ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ የተሰማ ሲሆን የኤሌክትሪክ መስመሮች በመጎዳታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የኃይል መቆራረጥ ችግር አጋጥሟቸዋል ተብሏል።

በሚኒሶማ ፉኩሺማ ከተማ ውስጥ የመደብሮች ሠራተኛ ዩኪ ዋታናቤ “በአነስተኛ መንቀጥቀጥ ተጀምሮ በድንገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ” በማለት ለአሳሂ ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች ተጨማሪ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እንደሚከሰት በማስጠንቀቃቸው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ እርምጃዎች አካል በሆኑ ድንኳኖች በተተከሉባቸው የመቆያ ማዕከላት ብዙ ነዋሪዎች እንደሚገኙ በመረጃው ተገልጿል።

በአገሪቷ ኢኮኖሚና በበጀት ፖሊሲ ኃላፊ ሚኒስትር የሆኑት ያሱቶሺ ኒሺሙራ ጉዳት ለደረሰባቸው ሀዘናቸውን ገልጸው፤ “መንግስት ድጋፍ ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ ማድረጉን ይቀጥላል” ማለታቸውን መረጃው አስታውሷል።