የሲዳማ ክልል የመልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

የካቲት 4 /2013(ኢዜአ) የሲዳማ ክልል የሕዝቡን የዘመናት ጥያቄዎች ለመመለስና ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የገለጹት የሀዌላ ቱላ-ወተራሬሳ-የዩ-ወራንቻ 84 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በይፋ በተጀመረበት መርሃ ግብር ነው።

ፕሮጀክቱ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን ግንባታው በ3 ዓመት ከ6 ወር ይጠናቀቃል ተብሏል።

በዩቴክ ኮንስትራክሽን የሚከናወነው የመንገድ ግንባታ ኢሲ እና ዩኒኮን ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ የተሰኙ አማካሪዎች የጥራት ቁጥጥሩን ይሰራሉ።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበትን ቡና ጨምሮ ሰብልና አትክልትና ፍራፍሬ አብቃይ አካባቢዎችን በማስተሳሰር ምርቶቹን በፍጥነት ለዓለምና ለአገር ውስጥ ገበያ ማድረስ ያስችላል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም የሲዳማና የኦሮሞ ማኀበረሰቦችን በማገናኘት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትስስራቸውን ማጠናከር ያስችላል ነው የተባለው።

መንገዱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ተደራሽነትም ያሰፋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት እንዳሉት ክልሉ ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ ለዜጎች የዘመናት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በአካባቢው ያለውን የኢኮኖሚ አቅም በመጠቀም ለአገር ብልጽግና ማዋል እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚፈለግበትን ሁሉ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ "ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶች የሚገኙበትን የደቡብና ደቡብ ምዕራብ፤ የምዕራብ ኢትዮጵያን ክፍል ከኢንደስትሪ ዞን፣ ከአጎራባች አገራት፣ ከአዲስ አበባና ሌሎች አቅጣጫዎች ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው" ብለዋል።

የዜጎች የመልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተካሄዱ ከሚገኙ ተግባራት የመንገድ ፕሮጀክቶች ሁነኛ ማሳያ ናቸው ብለዋል።

መንገዱ ከአካባቢው አልፎ አገራዊ ጠቀሜታ ካላቸው መንገዶች አንዱ መሆኑንም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቦኖ እንዳሉት መንገዱ ሲጠናቀቅ የወጪ ገቢን ለማሳደግና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ይረዳል።

የዩቴክ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ተክላይ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅ ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባልሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ የክልሉ መንግስት ለፕሮጀክቱ ስኬት የወሰን ማስከበርና ተያያዥ ጉዳዮች ችግሮችን በመፍታት እንዲተባበር ጠይቀዋል።

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም