በኦን ላይን ሊሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በወረቀት ይሰጣል-ትምህርት ሚኒስቴር

57

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2013 ( ኢዜአ) ትምህርት ሚኒስቴር በኦን ላይን ሊሰጥ የነበረውን የ2012ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በወረቀት እንደሚሰጥ አስታውቋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) በኦንላይን ለመስጠት የታሰበው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መፈተኛ ታብሌቶች በግዜ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ባለመቻላቸው ፈተናውን በወረቀት ለመስጠት መወሰኑን ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት የ2012 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና ከካቲት 29/ እስከ መጋቢት 2 2013 ዓ.ም እንደሚሰጥ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ሚኒስቴሩ በዛሬ መግለጫው እንዳለው የተፈታኞች ዲጂታል መታወቂያ ከየካቲት 22 እስከ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ይሰራጫል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ ፈተናውን በታብሌት ለመስጠት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ወደአገር ውስጥ ለማስገባት መዘግየት በማጋጠሙ የፈተናውን ቀን መወሰን እንዳልተቻለ ገልፀዋል።

ይሁንና የታብሌቱ መዘግየት ብቻም ሳይሆን ተማሪዎች ቴክኖሎጂውን ለመለማመድ የሚያስፈልጋቸውን ጊዜ በማጠሩ የ2012 ዓ.ም ተፈታኞችን በወረቀት ለመፈተን ውሳኔ ላይ ተደርሷል ብለዋል።

በዚሁ መሰረት የፈተናው ገለጻ የካቲት 26 ቀን፤ ፈተናው ደግሞ ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም የ350 ሺህ ተፈታኞች የዲጅታል ምዝገባ የተካሄደ ሲሆን በ1 ሺህ 185 የፈተና መስጫ ጣቢያዎች ሙሉ ለሙሉ የዲጅታል መሰረተ ልማት ተዘርግቷል ብለዋል።

በትግራይ ክልል የትምህርት መሰረተ ልማቶች በመውደማቸው በክልሉ የሚገኙ 12 ሺህ ተፈታኞች እስካሁን የዲጂታል ምዝገባ አለማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በተማሩበት ትምህርት ቤት በመሄድ ምዝገባ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ፈተናውን እስከሚጨርሱ የምገባና የመኝታ አገልግሎት ለመስጠት መወሰኑንም ገልጸዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተማሪዎችን በአራቱ ዩኒቨርሲቲዎች የማጓጓዙን ተግባር እንደሚወጣ በመግለጽ ወላጆች ልጆቻቸውን በመላክ ፈተናውን እንዲወስዱ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

መንግስት የትምህርት ዘርፉን ለመደገፍ በትግራይ ክልል 236 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በመተከል ዞን በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን የተማሪዎችን ስጋት ለማቃለል የስምንት ትምህርት ቤቶች ተፈታኞች ወደ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ሄደው እንዲፈተኑ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር በፈተና አሰጣጡ ላይ ለተፈጠረው መዘግየት ይቅርታ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም