የአፍሪካ አገራት የሱዳን መንግስት እያከናወነ ያለው አፍራሽ ተግባር ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ተጠየቀ

871

የካቲት 3/2013 (ኢዜአ)   የሱዳን መንግስት የዓለም አቀፍ ህግጋትን በተፃረረ መልኩ የግዛት ማስፋፋት፣ ዜጎችን የማፈናቀልና ንብረት የማውደም አፍራሽ ሥራዎች በመቀጠሉ የአፍሪካ አገራት ተጽእኖ ማሳደር እንዲችሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጠየቁ፡፡

ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑ የአፍሪካ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ ተደርጓል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ የሆኑት አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ ገለጻውን ሰጥተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጻ ያደረጉት በትግራይ ክልል እየተሰጠ ስለሚኘው ሰብአዊ ድጋፍ ፣ ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህደሴ ግድብ ድርድር፣ ቀጣይ ስለሚካሄደው የኢትዮጵያ ምርጫና የኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብ ዙሪያ ላይ ነው፡፡

በገለጻቸውም 26 የሚደርሱ አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሰብአዊ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል ህጋዊ ሰነዶችን አሟልተው በትግራይ ክልል ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ተገቢውን ማስረጃ፣ ውልና ፍቃድ ሳያገኙ በሰብአዊ ድጋፍ ስም በትግራይ ለመንቀሳቀስ ለሚፈለጉ አካላት ፍቃድና ዕውቅና እንደማይሰጥ አብራርተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ህዝባዊ ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞች ደመወዝ መከፍል መጀመሩን፣ የንግድ እንቅስቃሰየዎች እየተጀመሩ መሆኑን፣ ባንኮች አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው አካባቢው ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ እየተመለሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የህግ ማስከበር እርምጃው ከተጠናቀቀ በኃላ ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን የመልሶ ግንባታና የማቋቋም ስራ፤ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመወያየት ክልሉን ወደ ሙሉ ሰላም ለመመለስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በትግራይ ስለሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች አስመለክቶ አቶ ደመቀ እንዳሉት ከተዘረፉትና ጉዳት ከደረሰባቸው ሂጻጽና የሽመልአባ የስደተኛ ከምፖች የተበታተኑትን ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ካንምፖች ለመሰብሰብ መንግስት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

መጭውን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ ችግሮችን በመቋቋም ምርጫው ፍትሃዊ፣ነጻና ዴሞክራሳዊ እንዲሆን መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት አስረድተዋል፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢንርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘለት እቅድ መሰረት እየተገነባ እንደሚገኝ ገልፀው፤ በቀጣዩ ክረምት ግደቡ ወሃ እንደሚይዝም አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የደቡብ አፍሪካ መንግስት በተደራዳሪ ወገኖች ዙሪያ ያሉትን ክፍተቶች ለማጥበብ ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፍትሃዊነትና በተመጣጣኝ የውሃ የአጠቃቀም መርህ ላይ በመንተራስ ለጉዳዩ መፍትሄ ለመስጥት ፍላጎት ያላት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቋሚ ጻኃፊ አምባሳደር ወይንሽት ታደሰ በበኩላቸው የህግ የበላይነትን ለማሰከበር ኢትዮጵያ ሰራዊቷን ወደ ትግራይ ክልል ባሰማራችበት ወቅት ሱዳን የኢትዮጵያ ሉአላዊ ድንበር እንደጣሰች ገለጻ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት አቋም የያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የድንበር አለመግባባቱን በ1972 የማስታወሻ ልውውጥ ስምምነት ላይ ተመስርቶ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንሰተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በበኩላቸው የሱዳን መንግስት የዓለም አቀፍ ህግጋትን በተፃረረ መልኩ የግዛት ማስፋፋት፣ ዜጎችን የማፈናቀልና ንብረት የማውደም አፍራሽ ሥራዎች በመቀጠሉ የአፍሪካ አገራት ተጽእኖ እንዲያሳድሩ ጠይቀዋል።

የሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እስከሚፈታ ድረስ ሱዳን በኃይል ከያዘችው የኢትዮጵያ ግዛት እንዲትለቅም መጠየቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል ፡፡