ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል ኮሮና ለመከላከል የሚያግዝ የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ

42

ጋምቤላ፤ የካቲት 2/2013(ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከ865 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።

ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 50 የኦክስጅን ሲሊንደሮች፣ አምስት የኮሮና በሽታ የጽኑ ህሙማን ተኝቶ መታከሚያ አልጋዎችና 300 የጤና ባለሙያዎች መከላከያ አልባሳት ይገኝበታል ።

በኮሚሽኑ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሚስተር ኢሊጃ ቶዶሮቪስ የድጋፍ ርክክቡ ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት የኮሚሽኑ ደጋፍ ክልሉ ወረርሽኙን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ነው።

ኮሚሽኑ ካሁን በፊትም ለዚሁ ተግባር የሚውሉ ከሁለት ሚሊዮን 400ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ሁለት አንቡላንሶች እና ሌሎች የህክምና ቁሳቀሶች ድጋፍ ማድረጉን አውስተው በቀጣይም አጋርነቱን እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የህክምና ቁሳቁሶችን በተረከቡት ወቅት ኮሚሽኑ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ቀደም ሲልም ኮሚሽኑ ሁለት አንቡላሶችን ጨምሮ ያደረጋቸው ሌሎችም የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም