በተሰማራንበት የግንባታ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን እየተጋን ነው-የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን

1373

ጎባ፣ የካቲት 2/2013( ኢዜአ) በምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ ለመሆን እየተጉ መሆናቸውን ገለጹ።

በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የ184 አዳዲስና ነባር የመሰረተ ልማት ፕሮጄክቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

በዞኑ ጊኒር ከተማ የማርታ፣ ኦልአናና ጓደኞቹ ማህበር ኃላፊ ወጣት ፍራኦል መስፍን ለኢዜአ እንደገለጸው ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ ስድስት ጓደኞቹ ጋር ተደራጅተው ማህበሩን በመመስረት በግንባታ ስራ ተሰማርተዋል ።

በጊኒር ከተማ በ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የኮንትራት ውል ወስደው የገበያ ማዕከል ግንባታ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጿል።

በግንባታው ለሌሎች ከ100 ለሚበልጡ ወጣቶች ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥረናል” ብሏል።

“በግንባታ ዘርፍ ተሰማርተን በምናገኘው ገቢ ኑሯችንን ከመምራት ጎን ለጎን በዘርፉ የእውቀት ሽግግር እየፈጠርን ነው” ያለው ደግሞ የሂሩት፣ ሰናይትና ጓደኞቹ ማህበር ተወካይ ፋሲካ ግርማ ነው፡፡

በጊኒር ከተማ በወሰዱት የ700 ሺህ ብር የኮንትራት ውል የጎርፍ መውረጃ ቦይ ግንባታ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጿል ።

በተሰማሩበት የግንባታ ዘርፍ ሌሎች ወጣቶችም በስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ጎን ለጎን የእውቀት ሽግግር እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግሯል።

እንደ ማህበራቱ ሀላፊ ወጣቶች ገለጻ በተሰማሩበት የግንባታ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን እየተጉ ነው።

የጊኒር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሀሰን በከተማው በዘንድሮ በጀት አመት የህብረተሰቡን ፍላጎትና ችግር መሰረት በማድረግ በ32 ሚሊየን ብር የ16 መሰረተ ልማቶች ተቋማት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

” ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው በማህበራት የተደራጁ 567 ወጣቶች በመሰረተ ልማት ተቋማቱ ግንባታ ስራ እየተሳተፉ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

የምስራቅ ባሌ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሰለ አለሙ በዞኑ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የ184 አዳዲስና ነባር የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በግንባታ ላይ ካሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት መካከል የጠጠር መንገድ፣ የጎርፍ ማውረጃ ቦዮች፣ ድልድዮች፣ የማምረቻና መሸጫ ማእከላት፣ የገበያ ማዕከል፣ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።

እሰካሁን የ13 ተቋማት ግንባታ መጠናቀቁን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው የቀሪዎቹ ግንባታ ስራ እስከ በጀት አመቱ መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል ።

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተመረቁ ወጣቶች የተቋቋሙ ማህበራት በመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው” ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በክትትልና የድጋፍ ሂደት ዝቅተኛ የስራ አፈጻጸም ያስመዘገቡ የአስር ማህበራት የኮንትራት ውል መሰረዙን ተናግረዋል ።

የጊኒር ከተማ ነዋሪ ሁሴን ከድር በሰጡት አስተያየት በከተማው እየተገነቡ ባሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት የህዝቡ ጥያቄ እየተመለሰ መሆኑን ገልጸዋል።

“በከተማው የተገነቡ የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች፣ ድልድዮችና የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች ክረምት በመጣ ቁጥር ከሚገጥመን ስጋት አላቀውናል” ያሉት ደግሞ አቶ ጎሳ ወንበሪ ናው፡፡