ተመራቂዎች በሀገሪቱ የለውጥና የብልጽግና ጉዞ የራሳቸውን አሻራ ሊያሳርፉ ይገባል – ዶክተር አደም ቦሬ

1446

ሰመራ፣ የካቲት 2/2013 (ኢዜአ) ተመራቂ ተማሪዎች የሰላምና የአብሮነት እሴቶችን በማህበረሰብ ውስጥ በማስፋት በሀገሪቱ የለውጥና የብልጽግና ጉዞ የራሳቸውን አሻራ ሊያሳርፉ ይገባል ሲሉ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አደም ቦሬ አስገነዘቡ።

ዩኒቨርስቲው በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብር በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸው 1ሺህ 726 ተማሪዎች ዛሬ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አደም ቦሬ በስነ ስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ተመራቂዎች የሠላምና የአብሮነት እሴቶችን በማህበረሰብ ውስጥ በማስፋፋት በሀገሪቱ የለውጥና የብልጽግና ጉዞ የራሳቸውን አሻራ ሊያሳርፍ ይገባል ብለዋል።

“ተመራቂዎች ሀገራችሁ በተሰፋ ሰጪ የለውጥ ጉዞና ሊታለፍ በሚችሉ ፈተናዎች መሀል የምትገኝ መሆኗን አውቃችሁ የመፍትሄው አካል በመሆን የዜግነት ሃላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል ።

ዩኒቨርሲቲው በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብር አሰልጠኖ ዛሬ ካስመረቃቸው 1 ሺህ 726 ተማሪዎች መካከል 564ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል ።

“ተመራቂዎች የኮሮና ወረርሽኝ ተጽእኖ የፈጠረውን ከባድ ፈተና ተጋፍጣችሁ ለስኬት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የዩኒቨርስቲው ምክትል ቦርድ ሠብሳቢ አቶ ኡስማን መሀመድ ዩኒቨርስቲዉ ከመማር ማስተማር በተጨማሪ የአካባቢውን አርብቶ አደር በማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም በጥናትና ምርምር እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዩኒቨርሲቲው ለሚከናወኑ የመማር ማስተማርና የምርምር ስራዎች የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው በዩኒቨርሲቲው ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ላበረከቱት አስተዋጾኦ ምስጋና አቅርበዋል ።

በእለቱ በከፍተኛ ማእረግ የተመረቀችው ነጻነት ደለለኝ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ማህበረሰብ ያለው ሠላማዊና የአቃፊነት ሁኔታ ትምሀርቷን በትጋት እንድትማር ያደረጋት መሆኑን ገልጻለች ።

በተማረችበት ሙያ ህብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቷን አስታውቃለች ።