ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ወረዳ ለሚገነባው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረተ ድንጋይ አኖሩ

168

አምቦ፤ የካቲት 2/2013 (ኢዜአ) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ወረዳ ለሚገነባው የኢፈ ቦሩ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረተ ድንጋይ አኖሩ።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከሚያስገነባቸው ትምህርት ቤቶች አካል የሆነው ትምህርት ቤቱ የሚገነባው የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የትውልድ ስፍራ በሆነችው ቦሩ ጎረምቲ ቀበሌ ነው።

ትምህርት ቤቱ በሚገነባበት አካባቢ 10 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የተነሳ የአካባቢው ተማሪዎች ረጅም ርቀት ተጉዘው ለመማር ይገደዱ ነበር ተብሏል።

16 ክፍሎች የሚኖሩት ትምህርት ቤቱ በዉስጡ የአስተዳደር ህንጻ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ላቦራቶሪ፣ የቤተ መጽሀፍ፣ የኮምፕዩተር፣ ላብራቶሪ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ክፍሎች አሉት።

የትምህርት ቤቱ የመሰረተ ድንጋይ ማኖር መርሃ ግብር ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም