የመስኖ ልማት ኮሚሽን የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

61

የካቲት 1 ቀን 2013 (ኢዜአ) የተጓተቱ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የመስኖ ልማት ኮሚሽን ገለፀ።

የመስኖ ልማት ኮሚሽነሩ ዶክተር ኢንጂነር ወንድሙ ተክሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ በግንባታ ላይ ከሚገኙ 13 የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል ግንባታቸው ረጅም ጊዜ የሆናቸውን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።

በ2005 ዓ.ም ተጀምሮ የግንባታ አፈፃፀሙ 80 በመቶ የደረሰው የመገጭ ግድብ እንዲጠናቀቅ ከዋናው የሥራ ተቋራጭ በተጨማሪ ለተለያዩ ንዑስ ተቋራጮች መሰጠቱን ገልፀዋል።

17 ሺህ ሄክታር በማልማት 34 ሺህ አርሶ አደሮችና የጎንደር ከተማና አካባቢዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ ግድብ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሆነበት ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በጋራ የሚለሙበት ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍነው የጊዳቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የዋና ቦይ (ካናል) ሥራው ዘንድሮ ተጠናቆ በሚቀጥለው ዓመት ሥራ እንዲጀምር ጠቁመዋል።

"በኦሮሚያ ክልል አባያ ወረዳና በደቡብ ክልል ሎኮ አባያ ወረዳ አዋሳኝ ቦታዎችን በመስኖ የሚያለማው የጊዳቦ ግድብ ለግንባታው 1 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ወጥቶበታል" ብለዋል።

ኮሚሽኑ በተጨማሪ የጥገና ስራ የሚያስፈልጋቸውን የቆቦ፣ የፈንታሌና ሌሎች የመስኖ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለመስኖ ፕሮጀክቶች ትኩረት በመሰጠቱና የበጀት ችግሩ ስለተፈታ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና ወጪ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም