በገነቴ ከተማ በ37 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ

65

ደሴ ፤ የካቲት 1/2013(ኢዜአ)  በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ 37 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባ የገነቴ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት የከተማዋ አስተዳደር መጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ሰይድ እንደገለጹት በገነቴ ከተማ  የነበረው የመጠጥ ውሃ ችግር የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ቆይቷል።

ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት በተለያዩ ቦታዎች ጥልቅ ጉድጓዶች በመቆፈር ለአራት ጊዜ ቢሞከርም ውሃ ማግኘት ሳይቻል መቆየቱን አውስተዋል።

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በጥናት ተለይቶ በ2011 ዓ.ም. 37 ሚሊዮን ብር ተመድቦ  ግንባታው የተጀመረው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ አሁን ተጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

የውሃ ፕሮጀክቱ 200 ሺህ ሊትር ውሃ የሚይዝ ታንከር እንዳለው ጠቁመው፤ ከ13 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በተጠቃሚው ማህበረሰብ ዘንድ በቅርበት እንዲደርስም 11 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የቧንቧ መስመር በመዘርጋት ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ውሃ መስኖና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ሽመልስ በበኩላቸው የዞኑን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነቱን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁንም በተደረገው ጥረት ትናንት ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የገነቴ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት  አንዱ ትልቅ ስኬት እንደሆነ አስረድተዋል።

በክልሉ በገጠርና ከተማ የሚስተዋለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለማስተካከል መንግስት አቅሙ በቻለ ሁሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የአማራ ክልል ውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም 60 የውሃ ፕሮጀክቶች በክልሉ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ በወቅቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁም ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ህብረተሰቡ የውሃ ተቋማት እንዲገነቡ ከሚያቀርበው ጥያቄ በላይ ለተገነቡ የውሃ ተቋማት ጥበቃ በማደረግም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ከገነቴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ መሐመድ አሊ በሰጡት አስተያየት  የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት  ችግራቸው እንዲፈታላቸው  ለዘመናት ሲቀርቡ የነበረው ጥያቄ አሁን ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

''ውሃ ለማግኘት ከአንድ ስዓት በላይ በእግር ሲጓዙ ደግሞ ሴቶች ለተለያዩ ጥቃቶች ይዳረጉ ነበር፤  የተመረቀው የመጠጥ  ውሃ ፕሮጀክት ችግራችን ሁሉ ፈቶልናል'' ብለዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓት  የክልል፣ ዞንና ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች  ተገኝተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን  የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን አሁን ላይ 64 በመቶ መድረሱ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም