አርቲስት አሊ ቢራ በዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶቹ መልካም ትውልድ ለማፍራት አስተዋጽኦ አበርክቷል

171

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/ 2013 (ኢዜአ) "ዜጎች በየተሰማሩበት የስራ መስክ እንደ አርቲስት አሊ ቢራ ዘመን ተሻጋሪና ለትውልድ አርዓያ የሚሆን ተግባር ሊፈፅሙ ይገባል" ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ለክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ስራዎች እውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን በሙዚቃ ሕይወቱ ላይ ያተኮረ መጽሐፍም ተመርቋል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ "ሁላችንም በተሰማራንበት የስራ መስክ አርቲስት አሊ ቢራ የሰራውን ዘመን ተሻጋሪና የትውልድ አርዓያ የሆነ ስራ ማከናወን አለብን" ብለዋል።

ለክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ከፍተኛ ኒሻን ሽልማት በማበርከት ከ60 ዓመታት በላይ ለኦሮሞ ኪነ-ጥበብ እድገት ላበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ እውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

አርቲስቱ በሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ መልካም ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

አርቲስቱ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አብሮነትና ማህበራዊ ትስስር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው የተናገሩት ።

ለአብነትም "እናታችን አንድ ናት ማን አለያየን" በሚል ዜማ ስለ አገር አንድነትና የሕዝቦች አብሮነት ማቀንቀኑን አንስተዋል።

አሊ ቢራ በወቅታዊ ክስተቶች ሳይሸነፍ በጽናትና በብቃት ለረጅም ዓመታት በኪነ-ጥበብ ውስጥ ያሳለፈ መሆኑ አሁን ላለው ትውልድ ታላቅ ተምሳሌት እንደሚያደርገው ገልፀዋል።

"በኦሮሞ ባህል ማዕከል ውስጥ በአርቲስቱ ስም አንድ ቦታ በመሰየም የአርቲስቱን ስራዎች ሰብስቦ በማስቀመጥ ለትውልድ እንዲተላለፍ ይደረጋል" ብለዋልፕሬዚዳንቱ።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በበኩላቸው "ኪነ-ጥበብ የህብረተሰቡ መገለጫ ከመሆን አልፎ የባህል ዕድገትና የአገር አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ድርሻ አለው" ብለዋል።

ጥሩ ሰርተው ያለፉትን የማበረታታት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው፤ "ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ መሆኑን በተግባር ያሳየና ለሌሎች አርዓያ መሆን የቻለ ነው" ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙ አርቲስቶች ከአርቲስት አሊ ቢራ ብዙ ትምህርት መቅሰማቸውን ገልጸዋል።

ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም የተመሰረተውን የመጀመሪያው የኦሮምኛ ቋንቋ የኪነት ቡድን "አፍረን ቀሎ"ን በመቀላቀል ነበር የሙዚቃ ስራውን የጀመረው።

አርቲስቱ ከኦሮምኛ በተጨማሪ በአማርኛ፣ በሱማልኛ፣ በአፋርኛ፣ በሐረሪና በሱዳን ቋንቋዎች በርካታ ዘፈኖችን ተጫውቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም