ሀዋሳ ዓመታዊ የቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓል የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች

103
ሀዋሳ ሀምሌ18/2010 ሀዋሳ ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓል ለማክበርና የሚመጡ እንግዶች ለማስተናገድ መዘጋጀቷን በከተማዋ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ እንግዶችና ነዋሪዎች  ተናገሩ፡፡ ከትናንት ጀምሮ የእምነቱ ተከታዮች ከተለያዩ ከተሞች ወደ ሃዋሳ በመግባት ላይ የሚገኙ ሲሆን የከተማው ነዋሪዎችም እንግዶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዓሉን ለማክበር ከአዲስ አበባ ከቀናት በፊት እንደመጡ የተናገሩት ወይዘሮ አበባ ተስፋዬ የገብርኤልን ንግስ ለማክበር በዓመት ሁለት ጊዜ  እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡ የሃዋሳ ከተማ ህዝብ ደግና እንግዳ ተቀባይ እንደሆኑ ጠቅሰው ከተማዋ ሰላማዊ በመሆኗ  እንደልብ መንቀሳቃስ እንደቻሉም ገልጸዋል፡፡ ትራስፖርትና ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ተገቢውን  አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ በዓሉን ለማክበር ከአዲስ አበባ የመጡ አምስት ጓደኞቹን ተቀብሎ በማስተናገድ ላይ የሚገኘው ወጣት ቢኒያም ደምሴ በበኩሉ በከተማው ያለው ድባብ ሰላማዊና አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወጣት ቢኒያም እንዳለው ጓደኞቹም በከተማው ያለውን ድባብ እንደወደዱት ፣ በዓሉን በናፍቆት እንደሚጠብቁትና ከዋዜማው ጀምሮ ጥሩ ጊዜ እያሰለፉ ነው፡፡ "በዓሉን በተለያዩ ኃይማኖታዊ ስርዓቶች አክብረው እንዲመለሱ የሚጠበቅብኝን እያደረኩ ነው"ያለው ወጣቱ የከተማዋ ሰላም አስተማማኝ በመሆኑ ሃዋሳ ወደ ቀድሞ  ፍቅሯ መመለሷንም አመላክቷል፡፡ ሃዋሳ ከተማ ዓመታዊ የቅዱስ ገብርጌል ንግስ በዓል በሰፊው ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን የተናገረው ወጣት  መኳንንት ደሳለኝ ነው፡፡ ከዋዜማው ጀምሮ እንግዶችን እያስተናገደ ነው፡፡ በከተማው የሚገኙ ሆቴሎችና ማረፊያ ቦታዎች ተይዘው በማለቃቸው  ለእንግዶቹ ድንኳን ተክለው የማደሪያ ቦታ ማዘጋጀታቸውንም  ተገልጿል፡፡ ቄስ አበባየሁ ይርዳው በበኩላቸው በእንግዳ ተቀባይት የካበተ ልምድ ያላቸው የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ከሳምንት በፊት  አንስቶ ዝግጅት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ " ከትናንትና ጀምሮ እንግዶቻችንን እየተቀበልን እንገኛለን " ያሉት ቄስ አበባየሁ ከተማዋ ሰላማዊ በመሆኗ ከዚህ በፊት ድንገት ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር በበዓሉ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡ ዓመታዊ የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሀዋሳ  የሚመጡ የክርስትና እምነት ተከታዮች በታደሙበት ነገ  በድምቀት ይከበራል፡፡ የበዓሉ  አከባበር በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የሃዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማስታወቁን ኢዜአ ትናንት ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም