የባለፈው ስድስት ወራት አፈፃፀም አበረታች እና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ናቸው--ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች

ጥር 29/2013 (ኢዜአ) በባለፉት 6 ወራት በሁሉም መስኮች የተመዘገቡት አፈጻጸሞች አበረታች እና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ከተማዋ ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ በእጅጉ የሚያግዙ መሆናቸውን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

የገጠሙን ችግሮችንና ህዝባችን ያሣየንን ክፍተት በማረምና በማስተካከል ለህዝብ ተጠቃሚነት በትኩረት  መስራት እንደሚጠበቅ  ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ በዛሬው ዕለት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡

 በግምገማ ማጠቃለያ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹ ባለፉት ስድስት ወራት በከተማዋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ ህብረተሰቡን በተለያዩ ዘርፎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

 በተለይ ለረጅም ዓመታት ሲንከባለል የቆየው የመሬት ወረራ፣የኮንዶሚኒየም እና የቀበሌ መኖሪያ ቤቶችን ስርዓት ለማስያዝ የተሄደበት እርምጃ ፣አንገብጋቢ የሆኑ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ተጀምረው በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ፣ በከተማዋ ሰላማዊና የተረጋጋ እንቅስቃሴ እንዲሰፍን የተሰራው ስራ አበረታች መሆኑን ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

በነዚህ ሁሉ ዘርፎች ህብረተሰቡ ከለውጥ አመራሩ ጎን በመሰለፍ ያደረገው ትብብር ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ ስራዎች የተጀመረው ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ምክትል ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡

 በተጨማሪም የንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ትራንስፖርት ፣የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ፣የሴቶች እና ወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ፣ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ እና በሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል ።

በከተማዋ ሰላማዊና የተረጋጋ እንቅስቃሴ እንዲኖር ከህዝብም ከአመራሩም ተማክሮ የሚሰራ ገለልተኛ የጸጥታ ኮሚቴ መቋቋም መቻሉ ከታዩ ጥንካሬዎች አንዱ ተደርጎ እንደተገመገም ተገልፇል ።

 ባለፍት 6 ወራት ህዝቡ ለልማት ያለውን ፍላጎት ከጎናችን በመቆም አሣይቶናል ያሉት ወ/ሮ አዳነች የኑሮ ውድነቱና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች እያሉ  ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋፅኦ በማድረጋቸው አመስግነዋል።

ህብረተሰቡ ለመከላከያ ሰራዊት እና ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከመዋጮ ባለፈ ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር የተሰራው ስራ እና በኮቪድ-19 እና በበዓላት ወቅት ማዕድ በማጋራት ያሳየው ተሳትፎ ለሌሎች ስራዎች ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል ።

ህብረተሰቡን የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ ፣በልማት እንዲሳተፍ እና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ በአመራሩ በኩል ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የተሄደበት መንገድ አበረታች ነው ያሉት ወ/ሮ አዳነች በየደረጃው ያለ አመራር መካከል የተግባር እና የአስተሳሰብ አንድነት በመፍጠር ህዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በአግባቡ ለማድረስ ተቀናጅ እና ተናቦ መስራት አለበት ብለዋል፡፡

 በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም የነዋሪው አንገብጋቢ የሆኑ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ፣የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦት እና አምራቹን ከሸማቹ በቀጥታ ማገናኘት የሚችሉ ገበያ ማዕከላትን ማስፋፋት ላይ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የገጠሙንን ችግሮችና ነዋሪው በውይይታችን ያሣየንን ክፍተት በማረምና በማስተካከል እንዲሁም ለቀሪ ስድስት ወራት ያቀድናቸውን እና ካለፈው ተንጠባጥበው የቀሩ ስራዎችን አሟጠን ለህዝብ ተጠቃሚነትና እርካታ በርትተን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

 በመጨረሻም የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ በሰላማዊ ፣ፍጹም ዲሞክራሲያዊ እና እውነተኛ ምርጫ እንዲሆን ከተማ አስተዳደሩ ቅድሚያ ሰጥቶት ይሰራል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ በከተማዋ ያሉ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ህግ እና ስርዓትን አክብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሣስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም