ስምምነቱ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ከመስጠት ያለፈ ትርጉም አለው

98

ጥር 28/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያና በኡጋንዳ መካከል የተደረገው በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ፀድቆ ተግባራዊ ሲሆን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለፀ።

በአገራቱ መካከል በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትህ ትብብር ስምምነት የተፈረመው በ2011 ዓ.ም መጨረሻ ካምፓላ ላይ ነው።

ጥር 28/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በኩል ረቂቅ አዋጁ የተለያዩ ሂደቶችን በማለፍ ወደ ምክር ቤቱ የተመራ ሲሆን ዛሬ በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ በህግ ፍትህና ዴሞክራሲ እና የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ጥያቄዎች ተነስተዋል።

በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ እንደተቀመጠው በወንጀል ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ትብብር በህግ አስፈጻሚና በህግ ተርጓሚ ላይ የሚጣለው ሃላፊነት ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ለመወጣትና ስምምነቱን ለመተግበር ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምን ያህል ዝግጁ ነው የሚለው ከጥያቄዎቹ አንዱ ነው።

'የጋራ የፍትህ ትብብር ስምምነቱ ላይ የተፈጻሚነት ወሰንን የሚያሳይ ድንጋጌ ቢቀመጥም ይህ ትብብር ተፈጻሚነት የሚኖረው በሁሉም የወንጀል አይነቶች ነው ወይስ በተለዩ የወንጀል አይነቶች' የሚሉና መሰል ጥያቄዎች ቀርበዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮችም ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በህግ ጉዳዮች አለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክተር አቶ ዩሱፍ ጀማው በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገው ስምምነት በተለይ ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር ተያይዞ  እንደሚሰራበት አስረድተዋል።

ከኡጋንዳም ሆነ ከሌሎች አገራት ጋር ለሚደረጉ የፍትህ ትብብር ስምምነቶች በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ስምምነቱ በሁሉም የወንጀል አይነቶች ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን እንደ አገራቱ ፍላጎት 'ይበልጥ አስፈላጊ' በሆኑ የወንጀል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የታላላቅ ሀይቆች ዳይሬክተር አቶ ሞላ በለጠ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ያደረጉት ስምምነት የደህንነት ስራዎችን ለመስራት እንደሚያስችላቸው አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ በኩል ረቂቅ አዋጁን ለማጽደቅ እየተደረገ ያለው ሂደት እንዳለ ሆኖ በዑጋንዳ በኩል የተደረሰበትን ሂደት በቅርበት ተከታትለው እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

አገራቱ ያላቸው ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስምምነቱን ለማስፈጸም የተሻለ አቅም ይፈጥርላቸዋልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም