በኖኖ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ቡና፣ ዘይትና ማዳበሪያ ተያዘ

69
አምቦ ሀምሌ 18/2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ በህገወጥ መንገድ በግለሰቦች መጋዘን የተከማቸ ቡና፣ ዘይትና ማዳበሪያ  መያዙን የወረዳው ፖሊስ ገለጸ። የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ደበበ ዳዳለ ኢዜአ እንደገለጹት በህገወጥ መንገድ የተከማቸው ቡና፣ ዘይትና ማዳበሪያ ሊያዙ የቻለው ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ ነው። በግለሰቦች መጋዘን ሰሞኑን በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ  የተያዘው 74 ኩንታል ቡና፣ 144 ባለ 20 ሊትር ጀሪካን የምግብ ዘይት እና 50 ኩንታል ማዳበሪያ መሆኑን ገልጸዋል። በወረዳዋ ሲልክ- አምባ ከተማ በህገወጥ መንገድ ተከማችቶ የተያዘው ይኸው ንብረት ከ760 ሺህ ብር በላይ ግምት እንዳለው ጠቁመዋል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ኢንስፔክተር ደበበ አስታውቀዋል። የአካባቢው ነዋሪ ህገ ወጦችን በማጋለጥ ረገድ ያሳየው ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑንና በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ የሲልክ-አምባ ከተማ ነዋሪ አቶ ድሪባ አስረስ በሰጡት አስተያየት እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪ ህገወጥ ድርጊት ሲፈጸም በአፋጣኝ ለፖሊስ የመጠቆም ልምድ አዳብሯል። ይህም የዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም የሀገርንና የህብረተሰቡን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ሲፈጸም በቸልታ እንደማይመለከቱ ተናግረዋል፡፡ ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ፍቅረተ ሰፊሳ በበኩላቸው መንግስት የህብረተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት በድጎማ ከውጭ በሚያስገባቸው የፍጆታ ሸቀጦች ላይ ደባ የሚፈጽሙ  ህገወጦች በመያዛቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም