የዶክተር አምባቸው መኮንን ፋውንዴሽን በይፋ ተመሰረተ

1422

አዲስ አበባ፣ ጥር 27/2013 ( ኢዜአ) በቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ስም የተሰየመ ፋውንዴሽን በአዲስ አበባ ተመሰረተ፡፡

ትናንት ምሽት በተካሄደው የምስረታ ሥነ-ስርዓት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ እና የዶክተር አምባቸው ቤተሰቦችና ወዳጆች ታድመዋል፡፡

የፋውንዴሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ክንዳለም ዳምጤ ፋውንዴሽኑ በትምህርት፣ በጤናና በአረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት ያለመ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የሚከናወኑበትና የተሻለች አገርና መልካም ስብዕና ያለው ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ሥራ እንደሚሰራበትም ተናግረዋል፡፡

“በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተደራሽነትም ኅብረተሰቡ የቁጠባ ባህሉን እንዲያዳብር የሚያደርጉ ተግባራት በፋውንዴሽኑ ይከናወናሉ” ብለዋል።

በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን መደገፍና አገሩን የሚያለማ ሀቀኛ ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ በፋውንዴሽኑ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፋውንዴሽኑ ዓላማውን እንዲያሳካ የቦርድ አባል በመሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ዶክተር አምባቸው ለአገር አንድነትና ለሕዝቦች አብሮነት ሲታገሉ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ከንቲባዋ አርዓያነታቸውን በመከተል ከዘረኝነትና ጎጠኝነት ወጥቶ ለአገር አንድነት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የዶክተር አምባቸው ልጅ ወይዘሪት መአዛ አምባቸው ፋውንዴሽኑ እንዲመሰረት የፌዴራልና የክልል መንግስታት ላደረጉት ድጋፍ አመስግናለች፡፡

በተለይም ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለፋውንዴሽኑ ቦታ በመስጠትና ቤተሰቦቻቸው በደረሰባቸው ሃዘን እንዳይጎዱ ከጎናቸው በመሆን ላደረጉት ማፅናናትና ድጋፍ በማመስገን ፋውንዴሽኑ ግቡን እንዲያሳካ ድጋፉ እንዲቀጥል ጠይቃለች፡፡