ሰብአዊ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በፍጥነት የመታደግ ዘመቻ ላይ ነን ... ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

66

አዲስ አበባ፤ ጥር 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) “ሰብአዊ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በፍጥነት የመታደግ ዘመቻ ላይ ነን” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበይነ መረብ እየተካሄደ በሚገኘው በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ያለፈው የፈረንጆች ዓመት አፍሪካ በሰው ሰራሽ ግጭቶችና በተፈጥሮ አደጋዎች ማለትም በድርቅ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአንበጣ መንጋ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተፈተነችበት ዓመት እንደነበር አስታውሰዋል።

ችግሮቹ ከመኖሪያ ቦታ ለመፈናቀልና ለስደት እንዲሁም ለሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች አፍሪካዊያን እንዲዳረጉ ምክንያት ሆነው እንዳለፉ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያም ያጋጠሟትን አደጋዎች ለመቋቋም በምታደርገው ጥረት የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ያልተለያት መሆኑን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ከ19 አገራት የተውጣጡ ስደተኞችን በመቀበል በማስተናገድ ላይ እንደምትገኝ አብራርተዋል።

ያጋጠሙት ተደራራቢ የሆኑ ፈታኝ ሁኔታዎች በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስደተኞችን እና ተቀብለው እያስተናገዷቸው ያሉት ማህበረሰቦች ላይ የከፋ ችግር እንዳያስከትል መንግስት የጤና ተቋማትና አገልግሎቶችን፣ የንጽህና መጠበቂያ አቅርቦቶችንና መሰል አደጋ ለመቀነስ የሚያግዙ አቅርቦቶች ለማሟላት ርብርብ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በዚህም ሊያጋጥም ይችል የነበረን አደጋ በመቀነስ አድናቆት የተገኘበት ሥራ መሰራቱን ገልፀዋል። ኢትዮጰያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ህጎች መሰረት የስደተኞች ሁኔታ እና አያያዝ እንዲሻሻል፣ ሰብአዊ ክብራቸውና ፍላጎታቸው እንዲሟላ ግዴታዋን እንደምትወጣና ለዚሁም በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ትብብሯን አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆንዋን አረጋግጠዋል።

አያይዘውም ኢትዮጰያ ያጋጠማትን የሉዓላዊነትና የአገር አንድነት ፈተና ለመቀልበስ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ያደረችዉ የህግ የበላይነት የማስከበር ዘመቻ በወሳኝነት መጠናቀቁን ገልፀው፣ በቀጣይም የመልሶ ማቋቋም፣ የመልሶ ግንባታ እና ሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቁ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ “ሰብአዊ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በፍጥነት የመታደግ ዘመቻ ላይ ነን” ያሉት አቶ ደመቀ፤ በአጭር ጊዜ ብዙ ቦታዎችን መሸፈን የተቻለ ቢሆንም በቀጣይ ይህ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክቡር ለአፍሪካ ህብረት አባል አገራት፣ ለህብረቱ ሊቀመንበር ክቡር ፕሬዝዳንት ሲሪሊ ራማፎዛ፤ እንዲሁም ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ክቡር ሙሳ ፋቂ ማሐማት በአስቸካሪ ሁኔታ ውስጥ ለኢትዮጰያ ላሳዩት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም