ፓርላሜንተሪ ዲፕሎማሲን በማጠናከር የአገር ገጽታ ለመገንባት ይሰራል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

97

አዲስ አበባ፣ ጥር 26 /2013 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ተሳትፎ በሚጠይቀውን 'ፓርላሜንተሪ ዲፕሎማሲ' በማጠናከር የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት እንደሚሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ምክር ቤቱ በበኩሉ በፓርላሜንተሪ ዲፕሎማሲ ውጤታማ ስራዎች ለመስራት ፍላጎትና ዝግጁነት እንዳለው አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ ላለፉት ሶስት ቀናት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ለሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች ተወካዮች የተሰጠው የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

በዋናነት በፓርላሜንተሪ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮረው ስልጠናው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ የውሃ ፖለቲካ፣ የቀይ ባህርና አካባቢው ሁኔታና የኢትዮጵያ ሚና የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችንም አካቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለኢዜአ እንደተናገሩት የምክር ቤት አባላት የሚሳተፉበት የፖርላሜንተሪ ዲፕሎማሲ በሌሎች አገራት ውጤታማ ተግባራት ያከናውናል።

በተለይም መንግስት ከመንግስት የሚደረጉ ግንኙነቶችን ለማጠናከርና ግጭቶች እንዲፈቱ ለማስቻል ሚናው ጉልህ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዘርፉን እምብዛም እንዳልሰራችበት ገልጸው፤ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በተጠሪና በተቆጣጣሪ የወረቀት ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮችን በፊትለፊት ለመከወን ስራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

ሕዝብ የወከለው ምክር ቤት ከሌሎች አገራት ምክር ቤቶች ጋር ግንኙነት እንዲያጠናክር በማስቻል የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት፣ ድጋፍ ለማሰባሰብ ብሎም ዲፕሎማሲያዊ ክፍተቶችን ለመሙላት ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች እንዳለውም ነው የተናገሩት።

ይህን ዕውን ለማድረግ ደግሞ የጋራ ምክክርና ስልጠና አስፈላጊ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ላለፉት ሶስት ቀናት ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው ከሚቆጣጠራቸው ተቋማት አንዱ ከሆነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ስልጠናው በተለይም አሁናዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ ለመረዳት፣ በአፍሪካና በዓለምአቀፍ ደረጃ ያለችበትን ሁኔታ ለመረዳትና የምክር ቤቱ አባላት የጋራ ዕይታ ይዘው በሃላፊነት እንዲሰሩ እንደሚረዳ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በርካታ የለውጥ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህም መካከል የፓርላማ ዲፕሎማሲን ጠቅሰዋል።

"ፓርላሜንተሪ ዲፕሎማሲን ለማጠናክር ፍላጎትና ዝግጁነት አለን" ያሉት ዶክተር ነገሪ፤ ይህ የሚሳካው ደግሞ ጉዳዩ በዕውቀት ሲደገፍ እንደሆነ አመላክተዋል።

የተሰጠው ስልጠናው ውጤታማ በመሆኑ፤ የምክር ቤቱ አባላት የሁሉም ሕዝብ ተወካይ እንደመሆናቸው በፓርላሜንተሪ ዲፕሎማሲ የተሻለ ስራ እንዲሰሩ ያስችላል ብለዋል።

ከስልጠናው በኋላ የምክር ቤቱ አባላቱ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት በሚከፋፍሉ ሳይሆን አገርና ሕዝብን በሚያራምዱ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ከስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች በማካፈል የጋራ ዕይታ እንዲኖር መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም