የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

189

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2013(ኢዜአ) ከውጭ የሽብር ቡድን አባላት ተልዕኮ በመቀበል አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት በመፈጸም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 15 የሽብር ቡድን አባላት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ገለጸ።

አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የሽብር ቡድኑ ተጠርጣሪዎች የአፍሪካና የዓለም አቀፍ የዲፖሎማሲ ተቋማት መቀመጫ የሆነችውን የአዲስ አበባን በጎ ገፅታ ለማበላሸት በዝግጅት ላይ እንዳሉ የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች ፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።

የተደራጀ የህቡዕ ቡድን መስርተውና ከሽብር አቀነባባሪዎች የውጭ ተልዕኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የቆዩት አሸባሪዎች ለጥቃት ሊጠቀሙባቸው ያዘጋጇቸው ከፍተኛ የጦር መሣሪያዎችና ለፍንዳት ስራ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሳቀሶችና የተለያዩ ሰነዶች መገኘታቸውንም አስታውቋል።

የህቡዕ ቡድኑ በአዲስ አበባው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት፣ የጥናትና የመረጃ ማሰባሰብ ስራ ሲያካሂድ እንደቆየ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች መገኘታቸውንም መግለጫው ጠቁሟል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከህዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከሌሎች የሀገር ውስጥና የውጭ መረጃ ተቋማት ጋር በመሆን ጥብቅ ክትትልና የመረጃ ልውውጥ በማድረግ የታቀደውን የሽብር ጥቃት ማክሸፍ እንደተቻለም ነው የተገለጸው።

በአዲስ አበባ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት ለማድረስ በህቡዕ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል ጥቂቶቹ ከመያዛቸው በፊት በኤምባሲው ህንጻ አካባቢ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ይዘው ለድብቅ ሴራቸው ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም በክትትል መታወቁን መግለጫው አትቷል።

የሽብር ጥቃቱን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል የቡድኑን አባላት ሲመራ የነበረው የ35 ዓመቱ አሊ አህመድ አርዳይቶ ከፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።

ለአሊ አህመድ አርዳይቶ ለሽብር ጥቃቱ ማቀነባበሪያነት እንዲውል በአሥር ሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር እንደተላከለት ከተሰበሰቡ መረጃዎች ማረጋገጥ እንደተቻለም መግለጫው ጠቅሷል።

ግለሰቡ ጋር ግንኙነት የነበረውና የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በህቡህ ሲያሴር የቆየው መሃሙድ አብዱልቃኒ የተባለ ሌላ ተጠርጣሪም ከቀናት በኋላ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት በመኖሪያ ቤቱ የጦር መሣሪያዎች፣ ለፍንዳት ስራ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሳቀሶችና ሰነዶች መያዛቸውም ተገልጿል።

ሌላ ተመሳሳይ ተልዕኮ የተሠጠው ህቡዕ ቡድንም በሱዳን ካርቱም በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ ተመሳሳይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን የጠቆመው መግለጫው፤ መረጃውን ቀድሞ ያገኘውና ክትትል ሲያደርግ የቆየው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የግንኙነት መረቡን ለመበጣጠስ እንዲሁም ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝም ከሱዳን የመረጃና የደህንነት ተቋም ጋር በቅንጅት መሰራቱን ጠቁሟል።

ለህቡዕ የሽብር ቡድኑ መሪ ከውጭ አመራር የሚሰጠው ኑሮውን በስውዲን ያደረገው አህመድ እስማኤል የተባለ ግለሰብ ሲሆን፤ የሽብር ጥቃት ዕቅድ በማውጣትና ከሽብር ቡድኑ አባላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በአዲስ አበባ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኤምባሲ የደህንነት መረጃዎች እንዲሰበሰቡ አቅጣጫ ሲሰጥ መቆየቱንም መግለጫው ጠቅሷል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ በተመለከተ ከአውሮፓ፣ አፍሪካና እስያ የመረጃና ደህነንት ተቋማት ጋር የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥና ክትትል በማድረግ አህመድ እስማኤል በስውዲን ሀገር በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።

በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ሊቃጣ የነበረው የሽብር ጥቃት የከሸፈው አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከውጪና ከሀገር ውስጥ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ጋር የተቀናጀ ክትትልና የመረጃ ልውውጥ በማደረጉ መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀነባበረው የሽብር ሴራ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያና ከስዊድን በተጨማሪ በሌሎች ሀገራትም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።

ሌሎች ከሴራው ጋር ግንኙነት ያላቸውና በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ 21 ተጠርጣሪ ግለሰቦችንም በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ያመለከተው መግለጫው፤ በአገር ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ የሽብር ቡድኖቹ አባላትና ግብረ አበሮቻቸው በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

አገልግሎቱ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው አባላትን በመመልመል፣ የሽብር እቅድ በማውጣትና ኢላማዎችን በመለየት አዲስ አበባና ሱዳን በሚገኙት የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲዎች ላይ ጥቃቶችን ለመፈጸም ስምሪት ወስደው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበሩ ተጠርጣሪ የሽብር ቡድኖቹ አባላት እንዲያዙ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ትብብር አድርጓል።

በቀጣይም ህዝቡ ይሄን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደረግና የተለየ ነገር ሲመለከት በአካባቢው ላለ የፀጥታ አካል መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም