ፓን-አፍሪካኒዝምን መሰረት በማድረግ የአፍሪካን የጋራ እሴቶች ለማበልፀግ ተዘጋጅቻለሁ ...ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም

99

አዲስ አበባ፤ጥር 26/2013 (ኢዜአ) በኅብረቱ ኮሚሽነርነት ከተመረጡ ፓን-አፍሪካኒዝምን መሰረት በማድረግ በዘርፉ አፍሪካዊነትን የሚያጎለብቱ ስኬታማ ስራዎች ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ገለጹ።

አምስት የአፍሪካ አገራት ለአፍሪካ ኅብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽነርነት ዕጩዎቻቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያም ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያምን ለኅብረቱ ኮሚሽነርነት በዕጩነት አቅርባለች።

ፕሮፌሰሯ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የትምህርት ዝግጅታቸው፣ የስራ ልምድና የአመራርነት ብቃታቸው ለዕጩነት እንዳበቋቸው ገልጸዋል።በዘርፉ የሰሯቸው ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችና በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከወኗቸው ስኬታማ ስራዎችም እንዲሁ።

ፕሮፌሰር ሂሩት ለኅብረቱ ኮሚሽነርነት ከተመረጡ በአገራቸው ያስመዘገቡትን ውጤት በአፍሪካ ደረጃ በተሻለ አፈጻጸም ለመከወን ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተለይም ፓን አፍሪካኒዝምን መሰረት በማድረግ የአፍሪካን የጋራ እሴት ማበልፀግ ላይ እንደሚያተኩሩ አብራርተዋል።

በትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ በአፍሪካ ደረጃ ችግሮች የሚስተዋሉ መሆኑን ጥናቶች እንደሚያመላክቱ የጠቀሱት ፕሮፌሰሯ መፍትሄው ፓን አፍሪካኒዝም ላይ ያተኮሩ ስራዎች መስራት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በተለይም የአፍሪካ ወጣቶች ለአፍሪካ ዕድገት በጋራ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አፍሪካን የሚያዋህዱና የሚያስተሳስሩ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ስራዎችን ማስረጽ ላይ።የአፍሪካ የልህቀት ማዕከላትን በዘመናዊ መልኩ ማቋቋም፣ የትምህርት ስርዓቱን ለሁሉም የአፍሪካ አገራት በሚመች መልኩ ማቀናጀት፣ አፍሪካዊ ተፈጥሯዊ ክህሎቶችን ማበልፀግና የሴቶች እኩልነት ከሚሰሯቸው ስራዎች መካከል እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

የትምህርት ምዘና፣ ደረጃና ስርዓቱን ከየአገራቱ የአኗኗር ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም ማድረግም በዕቅድ ከያዟቸው ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ምርጫውን ካሸነፉ በህብረቱ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ አመራር እንደሚሆኑ የገለጹት ፕሮፌሰር ሂሩት፤ በዘርፉ ስኬታማ ስራዎችን ለመከወን ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ይህም ለሌሎች ሴት ምሁራን ተነሳሽነት የሚፈጥርና ብቃታቸውን የሚያጎላ በመሆኑ የዕጩነት ደረጃ ላይ መድረሳቸው በራሱ ለላቀ ስራ የሚያነሳሳ መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በሚገኙ 25 የአፍሪካ አገራት ኤምባሲዎች በመዘዋወር የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የቆዩት ፕሮፌሰር ሂሩት ኤምባሲዎቹ ላደረጉላቸው ቀና ምላሽና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

በተጨማሪም በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ውድድሩን እንዲያሸንፉ ባገኙት አጋጣሚ እያደረጉት ላለው ቅስቀሳና የማስተዋወቅ ስራም አመስግነዋል።

ዘንድሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በበይነ መረብ እንደሚካሄድ ታውቋል።

በመጪው ቅዳሜና እሁድ በሚካሄደው በዚህ ጉባዔም ለአፍሪካ ኅብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽነርነት ለሚወዳደሩ ዕጩዎች ድምጽ ይሰጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም