በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የስድስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

67
ሐረር ግንቦት 6/2010 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቀርሳ ወረዳ ትላንት ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ። በአደጋው ተጨማሪ ስድስት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ሲደርስ 30 በጎችም ሕይወታቸው ማለፉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ስዩም ደገፋ አስታውቀዋል። እንደኮማንደር ስዩም ገለጻ፣ የተሽከርካሪው አደጋ የደረሰው የቤት እንስሳትና ሰዎችን ይዞ ትናንት ከበደኖ ወረዳ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ይጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ በመገልበጡ ነው። የሰሌዳ ቁጥር  ኮድ 3 – 23171 (አ.አ) ኤፍ.ኤስ.አር የጭነት ተሽከርካሪ በወረዳው ገሌ ሚርጋ ገጠር ቀበሌ ሲደርስ መንገዱን ስቶ በመገልበጡ አደጋው ሊከሰት ችሏል። በአደጋው ረዳቱን ጨምሮ በተሽከርካሪው ላይ ተሳፍረው የነበሩ 6 ሰዎችና 30 በጎች ሕይወታቸው ወዲያውኑ ሲያልፍ በስድስት ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ኮማንደር ሰዩም ገልጸዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በጨለንቆና ድሬዳዋ ድልጮራ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የጠቆሙት ኮማንደር ስዩም፣ የሞቱት ሰዎችን አስክሬን ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው መውሰዳቸውን ተናግረዋል። ኮማንደር ስዩም እንዳሉት ለሕዝብ ትራንስፖርት ያልተፈቀደ የጭነት መኪና ሰዎችንና  የቤት እንስሳትን ከመጠን በላይ ጭኖ መንቀሳቀሱ ለአደጋው መከሰት አስተዋጽኦ አድርጓል። የመኪናው አሽከርካሪ ለጊዜው የተሰወረ ቢሆንም ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር በማዋል የአደጋውን ትክክለኛ መንስኤ ለማጣራት ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። ሕብረተሰቡ በተለይ ለሕዝብ ባልተፈቀደ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ ትራስንስፖት መጠቀም አደጋው የከፋ መሆኑን አውቆ ጥንቃቄ ማድረግ  እንዳለበት ኮማንደር ስዩም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም