የኢትዮ-ሱዳንን የድንበር ውዝግብ በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረዋል - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

118

አዲስ አበባ ጥር 25/ 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና የሱዳንን የድንበር ውዝግብ በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

አምባሳደር ዲና ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያና ሱዳንን የድንበር አለመግባባት በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

ይህንንም ለመደገፍ የአገራቱን ግንኙነትና የድንበር ሁኔታ በተመለከተ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ዐውደ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።

በአውደ ጥናቱ ለዘመናት የዘለቀው የአገራቱ ታሪካዊ የሁለትዮሽ፣ የሕዝብ ለሕዝብ፣ የእምነትና የባህል ግንኙነቶችን የተመለከቱ ጉዳዮች መነሳታቸውን ጠቁመው  ከዛ ጎን ለጎንም አሁን የገጠማቸው የድንበር አለመግባባትና እስካሁን ችግሮቹን ለመፍታት የተሄደባቸው ርቀቶች ትኩረት ተደርጎባቸዋል ብለዋል።

በተለይም በተቋማት ደረጃ የተከናወኑ ሥራዎችን በዝርዝር የተመለከተው ዐውደ ጥናቱ የኢትዮጵያ አቋም እስካሁን ሠላማዊ መንገድ የተከተለ እንደነበር ገልጸዋል።

 በአንጻሩ የሱዳን አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ፤ አሁንም የያዘችውን መሬት መልቀቅ እንደሚገባት የጋራ አቋም መያዙን ተናግረዋል።

ያም ሆኖ ኢትዮጵያ የጋራ ጥቅምን በማስከበር አለመግባባቱን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት 916 ስደተኞች ከተለያዩ አገራት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል።   

በትግራይ ክልልም የሠብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች እየተስፋፉና ከዚህ ቀደም ያልተደረሱ ሥፍራዎች እየተደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።  

"በክልሉ የሠብዓዊ ድጋፍ ኮሪደር አልተከፈተም" እየተባለ የሚሰራጨው መረጃም መሬት ላይ ካለው ሃቅ ጋር እንደማይመሳሰል ቃል አቀባዩ አንስተዋል።  

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ወደ ታንዛንያና ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ያደረጉት ጉብኝት ውጤታማ እንደነበረም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም