ዘመቻው እምቦጭን ከጣና የውሀ አካል ማጥፋት አይቻልም የሚለውን ተስፋ መቁረጥ የሰበረ ነው- አስተያየት ሰጭዎች

83

ባህር ዳር ኢዜአ ጥር 25/2013 እምቦጭን ለማሶገድ የተካሄደው ዘመቻ አረሙን ከጣና ሀይቅ የውሀ አካል ማጥፋት አይቻልም የሚለውን ተስፋ የመቁረጥ መንፈስ የሰበረ ነው ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

እምቦጭን ለማሶገድ በመንግስት አካላት የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የህብረተሰብ ክፍሎቹ አመላክተዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ዙሪያ ወረዳ የለንባ አርባይቱ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አርሶ አደር ማሬ ገዛኽኝ ለኢዜአ እንደገለጹት አካባቢው ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለውን እምቦጭ አረም ለማፋት ነዋሪው ተስፋ አስቆራጭ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

"አርሶ አደሩ ባለፉት ዘጠኝ ዓመት አረሙን ከሃይቁ ለማስወገድ ያለምንም ክፍያ ሲለፉ መቆየቱን አስታውሰዋል።

"ይሁንና አረሙ እየተስፋፋ የእርሻ መሬቶችን በመውረርና የአሳ ሃብትን በማጥፋት ጎጅነቱ እየጨመረ በመምጣቱ በተለይ አረሙን ከሀይቁ የውሀ ክፍል ማጥፋት አይቻልም የሚል ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አሳድሮ ነበር" ብለዋል ።

በዚህ ዓመት በመንግስት አካላት ለጉዳዩ በተሰጠ ልዩ ትኩረትና ድጋፍ አረሙን ለማሶገድ በተካሄደ ዘመቻ  አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

በቀን እስከ 3 ሺህ 600 ሰው በተሳተፈበት ዘመቻ አረሙን ከሀይቁ የውሃ አካል ማጥፋት እንደሚቻል የተረጋገጠበት ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል ።

በዚህ አመት መጨረሻ ድረስ አረሙን ከአካባቢያቸው ሙሉ ለሙሉ አሶግደው ለማጠናቀቅ እየተጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"እምቦጭ የሰብል ምርታማነትን በመቀነስ ጉዳት አድርሶብናል" ያሉት ደግሞ በፎገራ ወረዳ የናበጋ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለማየሁ ገረመው ናቸው።

"ከዚህ በፊት አረሙን በዘመቻ  የማንሳት ስራ ቢከናወንም ተገቢው ክትትል ባለመኖሩ ውጤት ሳይመጣ ቆይቷል" ብለዋል።

በዚህ ዓመት ከመንግስት አካላት በተሰጠው ትኩረት አረሙን ለማሶገድ በተካሄደ ዘመቻ ጠንከራ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ መደረጉ በአጭር ጊዜ አመርቂ ስራ መሰራቱን አመልክተዋል።

አርሶ አደሮች ተደራጅተው አረሙን የማፅዳት ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው አሁን ላይ ቀሪውን አረም የመልቀም፣ የተወገደውን ለማቃጠል የማዳረቅና የማገላበጥ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"እምቦጭን ለማውገድ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም በዚህ ዓመት በተካሄደ ዘመቻ የታየው ድጋፍና የተገኘው ወጤት የተለየ ነው" ያሉት ደግሞ የጤዛ አምባ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አርሶ አደር አቻም ጠጋ ናቸው።

"በዘመቻው አርሶ አደሩን በ1 ለ 25 በቡድን በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገባ በመደረጉ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አረሙን  ማጽዳት ተችሏል፤ አረሙ ከሀይቁ ወሀ አይጠፋም የሚለውን ተስፋ መቁረጥ ያስቀረ ውጤትም ተገኝታል" ብለዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ባንቲሁን መኮንን በበኩላቸው የዚህ ዓመት የእምቦጭ አረም ማሶገድ ዘመቻ የአይቻልምን ስሜት የሰበረ እንደነበር ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ባለፉት ዓመታት አረሙን ለማሶገድ ያለምንም እረፍት ሲሰራ ቢቆይም ለውጥ ባለማየቱ ተስፋ ቆርጦ እንደነበር አስታውሰዋል ።

"ዘንድሮ የተካሄደው አረሙን የማሶገድ ዘመቻ አርሶ አደሩን ከተስፋ መቁረጥ ታድጎታል" ብለዋል።

"በዘንድሮ ዘመቻ አርሶ አደሩ በገንዘብ ክእንዲደገፍ ተደርጓል፤ በተሰራውም ስራ አበረታች ውጤት ተገኝታል" ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው  በዞኑ አረሙ ከተስፋፋባቸው 18 ቀበሌዎች ውስጥ በ10ሩ ሙሉ በሙሉ መወገዱን አስታውቀዋል።

በዘንድሮ ዘመቻ በጣና ሃይቅ የውሀ አካልና ዙሪያ አካባቢው በ4 ሺህ 300 ሄክታር ላይ ከተስፋፋው የእምቦጭ አረም 94 በመቶ መወገዱ ታውቋል ።

በዘመቻው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም