በህገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 10ሺህ ዶላር በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተያዘ

137
አዲስ አበባ ሐምሌ 18/2010 በህገወጥ መንገድ ከሃገር ሊወጣ የነበረ 10ሺህ የአሜሪካን ዶላር በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ። ገንዘቡ ትናንት ሐምሌ 17 ቀን 2010 ዓም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል ወደ ውጭ ሊወጣ ሲል በተደረገ ፍተሻ መያዙ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ግለሰቦች በየቤታቸው ያከማቹትን የውጭ ምንዛሬ በባንክ እንዲመነዝሩ ጥሪ ማስተላለፉን ተከትሎ በህገወጥ መንገድ ገንዘብ ወደ ውጭ ለማስወጣት እየሞከሩ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንም እነዚህን ህገወጦች ለመከላከል በልዩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በዚህም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል በህገወጥ መንገድ ከሃገር ሊወጣ የነበረ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላርና 3ሺህ950 የኢትዮጰያ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል። እየተደረገ ያለውን ፍተሻና ቁጥጥር ህብረተሰቡ እየደገፈ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ኤፍሬም ከዚህ በፊት በፍተሻ ጣቢያዎች በርካታ ህገ ወጥ ገንዘብና ሌሎች ውድ እቃዎች በህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት ከአገር ሊወጣ ሲል መያዙን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩ ሀሰተኛ የኢትዮጵያ የብር ኖቶች በፍተሻ እየተያዙ መሆኑን ገልጸዋል። የውጭ ምንዛሬ በቤታቸው ያከማቹ ግለሰቦችም ከአገር ከማስወጣት ይልቅ ገንዘባቸውን በባንክ በመመንዘር የቀረበውን አገራዊ ጥሪ በመቀበል የራሳቸውን ከህገወጥ ድርጊት መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ህገ ወጦችን በማጋለጥ ረገድ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም