የማይስ ኢትዮጵያ ዘርፍ መለያ ዓርማ ይፋ ሆነ

1629

አዲስ አበባ፣ ጥር 25/2013 ( ኢዜአ) በጉባኤዎች፣ ስብሰባዎችና ዐውደ ርዕዮች ሁነቶችን ያካተተው የማይስ ኢትዮጵያ ዘርፍ መለያ ዓርማ ይፋ ሆነ።

በማይስ ቱሪዝምን የሚመራና የሚያስተባብር የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮም ተመሰርቷል።

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተካሄደው ምስረታና ይፋ ማድረግ ስነ-ስርዓት ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ “ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት ምድረ ቀደምት አገርና የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ማዕከል ናት” ብለዋል።

” ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም አየር መንገድ አላት፤ በመዝናኛና ስፖርት ትልቅ አቅም ያላት በመሆኑ ይህን ዕድል ለማይስ ቱሪዝም መጠቀም ተገቢ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ከባህል፣ ተፈጥሮና ታሪክ ቱሪዝም ፀጋዎች ባሻገር ትልቅ አቅም ስላላት ዕድሉን መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

“ያለንን ፀጋዎች በአግባቡ ለመጠቀም በ10 ዓመቱ ዕቅድ ቱሪዝም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ አካታች ፈጠራ የታከለበት ኢትዮጵያን የማስተዋወቅና ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ዛሬ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮም በአግባቡ ከተሰራበት ብዙ ርቀት የሚያሻግር ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ አለው” ብለዋል።

ማይስ ኢትዮጵያ ጉባዔዎች፣ የጉዞ ማበረታቻዎች፣ ኮንፈረንስና የኤግዚቢሽንን ሁነቶችን ያካተተ የቱሪዝም ዘርፍ ሲሆን ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት መገኛና ሁነቶችን አስተናጋጅ በመሆኗ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን አቅዳለች።

በዚህም እንግዶችን ለመቀበልና ሁነቶች እንዲከናወኑ አጋር አካላትን በማስተባበር ዘርፉን የሚመራ በቱሪዝም ኢትዮጵያ ስር የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ የተሰኘ ተቋም ተመስርቷል።

ተቋሙም “በምድረ ቀደምት እንገናኝ” የሚል መሪ ቃል እንደሚኖረው ተገልጿል።

በመድረኩ ለዚህ ዘርፍ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች ዕውቅና ተሰጥቷል።