ወጣት ምሩቃን ማህበረሰባዊ ችግርን የሚፈቱ ፈጠራዎች ላይ ለመስራት መትጋት አለባቸው- ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ

63
አዲስ አበባ ሐምሌ 18/2010 ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ምሩቃን ያደጉ ሀገራትን ቴክኖሎጂዎች መቅዳትንና ማላመድን ጨምሮ ማህበረሰባዊ ችግርን የሚፈቱ ፈጠራዎች ላይ ለመስራት መዘጋጀት አንዳለባቸው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ። ፕሬዝዳንቱ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነው የተመረቁ ከ400 በላይ የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በብሄራዊ ቤተ መንግስት አግኝተው አነጋግረዋል። የዘንድሮ የሜዳሊያ ተሸላሚ ምሩቃን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀደም ሲል ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን በመጎብኘት ላይ ከመሆናቸውም በላይ ከከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋርም ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። በዚህም መሰረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ከህዘብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሙፈሪሃት ካሚል ጋር ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና የኢትዮጵያ አየር መንገድንም ጎብኝተዋል። በትናንትናው እለት ደግሞ በብሄራዊ ቤተ መንግስት ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር ሀሳብ ተለዋውጠዋል። በዚህ ወቅትም ፕሬዝዳንቱ  እንዳሉት፤ ምሩቃኑ የተማረ ሰው የአንዲት አገር ሁለንተናዊ እድገት መሰረት መሆኑን ተገንዝበው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድና የፈጠራ አቅማቸውን በማሳደግ ኅብረተሰባቸውን ለማገልግል መዘጋጀት አለባቸው። "ምሩቃኑ ከራሳቸው አልፈው አገራቸውንና ወገናቸውን ለማገልገል መዘጋጀት አለባቸው ሲባል በትምህርት ቤት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ስራ ላይ ማዋልን ይጠይቃል" ሲሉም ነው ፕሬዝዳንቱ ያስገነዘቡት። "መማር ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ እውቀት የህይወት መምሪያ ቁልፍ መሆኑን በመረዳት ጊዜ ሳታባክኑ ነገ እሰራዋለሁ ብላችሁ ሳትዘናጉ አሁኑኑ ተግባር ላይ አውሉት" ሲሊ ምሩቃኑን መክረዋል። በአለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ሰዎች ስኬት ጀርባ ያላሰለሰ ጥረት እንዳለ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ወጣቶች ትልቅ ህልም ብቻ ሳይሆን ለህልማቸው መሳካት ሌት ተቀን በርትተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። ችግሮችን ከመፍራት ይልቅ እንደ እድልና መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መፍትሄ መፈለግ፣ ተወዳዳሪና ለሌሎች አርዓያ መሆን፣ የአገሪቱን ፍላጎት በማገናዘብ የኅብረተሰቡን ችግሮች በመንፈሰ ጠንካራነት መፍታት የወጣቶች የእለት ተዕለት ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አስረድተዋል። መንግስት በሳይንስና ቴክኖሎጂ  ፈጠራ እንዲሁም በጥናትና ምርመር ዘርፍ የሚያተኩሩ ወጣቶችን ለማበረታታትና ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። ዶክተር ሙላቱ አንዳሉት ኢትዮጵያ ዘመናዊ ግብርና መተግበር አቅቷት ለዘመናት በኋላቀር አስተራረስ የኖረችው በዶማ ከማረስ በበሬ ማረስን የመጨረሻ እርካታ አድርጎ ከመውሰድ የመነጨ መሆኑን ጠቁመው፤ ወጣቶች በሚያገኙት አዲስ ስኬት ሳይኩራሩና ሳይረኩ ለሌላ ተጨማሪና አዲስ ስኬት የበለጠ መነሳሳት አለባቸው። አክለውም ወጣቶች መልካም ሰብዕና የተላበሱ በሥነ ምግባራቸው ምስጉን በመሆን ኅብረተሰባቸውን በቅንነት ማገልገልና "ሰው የዘራውን ያጭዳል" እንዲሉ ለነገ ማንነታቸው ዛሬ መጥፎውን ከጥሩ ለይተው እንዲሰሩም መክረዋል። "በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ሆናችሁ የኢትዮጵያ ህልም የሆነው አንድነት፣ ሰላም፣ መልካም አስተዳደር መስፈን እንዲሁም ልማቱ ከግብ እንዲደርስ የእናንተ ሃላፊነት የጎላ መሆኑን ሁሌም መዘንጋት የለባችሁም" ብለዋቸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም