በሻምፒዮናው በኬኒያዊው አትሌት የታየው ጠንካራ ፉክክር ቀጣይ መሰራት ያለበትን የቤት ስራ ያሳያል- ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ

1470

ጥር 23/2013 (ኢዜአ) በጃንሜዳ ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በኬኒያዊው አትሌት የታየው ጠንካራ ፉክክር በቀጣይ መሰራት ያለበትን የቤት ስራ የሚያሳይ ነው – የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ። የጃንሜዳ ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዛሬ ተካሄዷል።

38ኛው የጃንሜዳ ዓለም አቀፍ  አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ የቦታ ለውጥ አድርጎ በሱሉልታ ከተማ ስያሜውን እንደያዘ ተካሄዷል።

ሻምፒዮናው በአዋቂ ሴቶችና ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር፣ በዱላ ቅብብል 8 ኪሎ ሜትርና እንዲሁም የአንጋፋ አትሌቶች 8 ኪሎ ሜትር መካከል ነው የተካሄደው።

በዚህ ሻምፒዮናው እንዲሳተፉ ከተጋበዙ የውጭ አገራት መካከል ከደቡብ ሱዳን ሁለት አትሌትና ከኬኒያ አንድ አትሌት የተሳተፉ ሲሆን የሱዳን አትሌቶች ግን ለመምጣት አለመገኘታቸው ታውቋል።

በጃንሜዳ ከተካፈሉ የሶስት የውጭ አገራት አትሌቶች መካከል በ10 ኪሎሜትር አዋቂ ወንዶች የተካፈለው          ኬኒያዊው አትሌት ዳንኤል ሲሚዩ ውድድሩንም በሁለተኝነት በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

አትሌቱ ውድድሩ ሊጠናቀቀ 50 ሜትር አካባቢ እስኪቀረው ድረስ ከፊት ሆኖ እየመራ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻው ሰዓት የአማራ ማረሚያ አትሌት በሆነው አትሌት ንብረት መላክ ተቀድሞ ሁለተኛ መውጣት ችሏል።

ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ተሬሳ ቶሎሳ ደግሞ ሶስተኛ  በመሆን  የነሐስ  ሜዳሊያ ማግኘት ችሏል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ ኬኒያዊው አትሌት ያሳየው ፉክክር ጠንካራና ለማሸነፍም ተቃርቦ እንደነበር ገልጻለች።

”ኢትዮጵያ ስላዘጋጀችው ብቻ ኢትዮጵያዊያን አትሌት ብቻ ማሸነፍ አለባቸው ባይባልም፤ ብንሸነፍ ለአትሌቶችም ሆነ ለአመራሩ ጥሩ ስሜትን የሚፈጥር አልነበርም” ብላለች።

ኬኒያዊው አትሌት ያሳየው ብቃት ግን ቀጣይ ለጠንካራ ራስን ማዘጋጀት እንደሚገባ የሚያሳይ ነው ስትል ተናገራለች።

በ38ኛው የጃንሜዳ ዓለም አቀፍ ሻምፒዮና አንጋፋ አትሌቶችን ሳይጨምር አምስት ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን አማራ ክልል በአጠቃላይ ውጤት በአዋቂ ሴቶች፣ በወጣት ወንዶችና ሴቶች የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ          ከተዘጋጁ አምስት ዋንጫዎች ሶስቱን መውሰድ ችሏል።

መከላከያ በአዋቂ ወንዶች ዋንጫ መውሰድ የቻለ ሲሆን ፌዴራል ማረሚያ ስፖርት ክለብ ደግሞ በድብልቅ የዱላ ቅብብል አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።