የባቡር ሀዲድ ማያያዣና የነዳጅ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ነዳጅ ለማጓጓዝ የምታወጣውን ወጪና የጊዜ ብክነት ይቀንሳል ተባለ

1926

ጥር 23/2013 (ኢዜአ) የባቡር ሀዲድ ማያያዣና የነዳጅ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ነዳጅ ለማጓጓዝ የምታወጣውን ወጪና ለማጓዝ የሚወስደውን ጊዜ እንደሚቀንስ ተገለጸ።

ፕሮጀክቱ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ አቅምን ይጨምራልም ተብሏል።

የአዋሽ ነዳጅ ማቆሪያ የባቡር ሀዲድ ማያያዣና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ዛሬ የተጀመረ ሲሆን በአፋር ክልል ዞን ሶስት አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አዋሽ ሰባት ከተማ የፕሮጀክቱ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከናውኗል።

የፕሮጀክቱ ወጪ 2 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር ሲሆን በአንድ አመት ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ  ፕሮጀክት የግንባታ ወጪው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው።

በፕሮጀክቱ የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ መቀሌ የባቡር መስመርን ከአዲስ አበባ፣ ሰበታ ሜኤሶ ደንወሌ የማያያዝ ስራ ይከናወናል።

የአዲስ አበባ ደንወሌ የባቡር መስመርን ከአዋሽ የነዳጅ ማቆሪያ ጋር የማያያዝና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማቶችን የመገንባት ስራም በፕሮጀክቱ የተካተቱ ስራዎች ናቸው።

በተጨማሪም የባቡር መተላለፊያ ፌርማታ ግንባታ የሚከናወን ሲሆን ፌርማታው የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት የሚያገለግል ነው።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም ኢትዮጵያ ለነዳጅ አቅርቦት በየዓመቱ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ታወጣለች ብለዋል።

ነዳጅ ለማጓጓዝ የምትጠቀመው የጭነት መኪናዎችን እንደሆነና ይሄም ከወጪና ጊዜ አንጻር ብክነት እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ስራ ሲጀመር የነዳጅ ጫኝ የባቡር ፉርጎዎች ነዳጅ ማጓጓዝ ሲጀምሩ ወጪን በመቀነስ እንዲሁም ለቀናት ነዳጅ ለማጓጓዝ የሚወስደውን ጊዜ ወደ ሰዓታት እንደሚያወርደው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ ጅቡቲ እንዲሁም የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ መቀሌ የባቡር መስመሮች አገልግሎት አሰጣጥ አቅምን የሚያጎለብት ነው ብለዋል።

 ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅና በሚፈለገው የጥራት ደረጃ እንዲከናወን ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል ወግሪስ በበኩላቸው የባቡር ሀዲድ ማያያዣና የነዳጅ ፕሮጀክቱ ከትራንስፖርት ጠቃሜታው ባለፈ የጎላ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

የባቡር ሀዲድ ማያያዣና የነዳጅ ፕሮጀክቱ ተቋራጭ የቻይና ሲቪል ኢንጅነሪግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ጉዎ ቾንግፌንግ ኮርፖሬሽኑ ያለውን አቅም እውቀት ተጠቅሞ ፕሮጀክቱን በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የአፋር ክልል የመንገድና ትራንስፖርት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጣሃ መሐመድ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ ያሉ የወሰን ማስከበር ጉዳዮች እንዲጠናቀቁ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅና ወደ ስራ ሲገባ ከቻይና የተገዙ 110 የነዳጅ ጫኝ የባቡር ፉርጎዎች በባቡር መስመሩ አገልግሎት በመስጠት የነዳጅ ጫኝ ቦቴ መኪናዎችን አገልግሎት ይተካሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል።

የአዋሽ ነዳጅ ማቆሪያ የባቡር ሀዲድ ማያያዣና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት አሰሪ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሲሆን የፕሮጀክቱ ተቋራጭ ደግሞ የቻይና ሲቪል ኢንጅነሪግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ነው፡፡

የፕሮጀክቱ አማካሪ የቻይና ኢንተርናሽናል ኢንጅነሪግ ኮንሰልታት ኮርፖሬሽን እንደሆነ ተገልጿል።