በከተሞች ከስምንት መቶ ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጠረ

64

ጥር 23/2013 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ከተሞች ከስምንት መቶ ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን መሪ ወይዘሮ አቦዘነች ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት ስድስት ወራት በአገሪቱ ከተሞች የስራ እድል ፈጠራ ከእቅድ በላይ ተከናውኗል።

በግማሽ አመቱ ተመራቂ ተማሪዎችን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 668 ሺህ 247 ዜጎች የስራ ዕድል እንዲያገኙ ታቅዶ ለ 871 ሺህ 383 ጊዚያዊና ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው በማኑፋክቸሪግ፣ በጨርቃ-ጨርቅ ፣ በቆዳ ስራና በኮንስትራክሽን ዘርፎች ነው።

የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከልም 41 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ግንባታቸው የተጠናቀቁ 1ሺህ 858 ሼዶችን ለተጠቃሚዎች መሰጠቱን ወይዘሮ አቦዘነች አያይዘው ይገልጻሉ፡፡

እንደ ቡድን መሪዋ ገለፃ በበጀት ዓመቱ ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ ድጋፍ ለማድረግ ከቁጠባ የተሰበሰበ 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብድር ተስጥቷል።

በክልሎች የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም አውደ-ርዕይን በማዘጋጀት የገበያ ትስስር  መፈጠሩንም ያስረዳሉ።

ኢንተርፕራይዞቹ እያመረቱት ያለው ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸሻለ መምጣቱን የገለፁት ወይዘሮ አቦዘነች ህብረተሰቡም በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን የመግዛት ባህሉን ማዳበር እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

ዜጎች በመንግስት የሚፈጠረውን የስራ ዕድል ብቻ ሳይጠብቁ በራሳቸው የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም