ተመራቂዎች ሀገራዊ የለውጥና የብልጽግና ጉዞን ወደ ፊት ማራመድ እንደሚጠበቅባቸው ተመለከተ

1569

ጋምቤላ ጥር 23/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ለማራመድ በሚደረገው ጥረት ከተመራቂ ተማሪዎች የላቀ ድርሻ ይጠበቃል ሲሉ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙዬል ክፍሌ አስገነዘቡ።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች በመደበኛና በተከታተይ መረሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 229 ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ዛሬ አስመርቋል ።

ሚኒስትር ዴኤታው በምረቃ ስነ -ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ  ልታስመዘግብ  ላቀደቻቸው የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና ግቦች እውን መሆኑን ሁሉም በሰለጠነበት የሙያ መስክ በአንድነት ተባብሮ ሊሰራ ይገባል።

“በተለይም ተመራቂ ተማሪዎች ሀገሪቱ የተሰነቁ የብልጽግናና የልማት እቅዶች ተግባሪ አካል ለመሆናቸው በመታደላችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል” ብለዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የነበሩ ክፈቶችና የኮሮና ወረርሽኝ ተጽዕኖችን በመቋቋም ለምረቃ መብቀታቸውን አድንቀዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ  ተገኝተው  ባስተላለፉት መልክት “በክልሉ ብሎም  በሀገሪቱ የታለመውን  የእድገትና  የብልጽግና ጉዞ እውን ማድረግ የሚቻለው ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ሲቻል ነው” ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን የሰው ኃይል ፍላጎት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የጀመረውን የሰብአዊ ሀብት ልማት አጠናክሮ ሊቀጥል እንሚገባ አስገንዝበዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን ዩኒቨርሲቲው በክልሉ ያለውን የዓሳ፣ የማዕድንና በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን እምቅ ሀብት በምርምር በማገዝ ወደ ልማት እንዲለውጥ በማድረግ ረገድ ድርሻውን እንዲወጣም  አስገንዝበዋል።

የእለቱ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው ቆየታቸው የቀሰሙትን ሙያ ካላቸው አፍላ ጉልበት ጋር በማቀናጀት እራሳቸውና ሀገራቸውን ለመለወጥ ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ የኒቨርሲቲው ለድስተኛ ጊዜ በዛሬው እለት ያስመረቃቸው

1 ሺህ 229 ተማሪዎች በ27 የትምህርት መስኮች በመደበኛና በተከታታይ መርሀ ግብር በመጀመሪና በሁለተኛ ድግሪ የተሰጣቸውን ስልጠና  በአግባቡ ያጠናቀቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል 1 ሺህ 184ቱ በመጀመሪያ ዲግሪ 45ቱ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከአጠቃለይ ተመራቂዎች መካለከልም 424ቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ተማሪ እመቤት ተካ በሰጠችው አስተያየት በዩኒቨርሰቲ ቆይታዋ የኮቪድና ሌሎች ጫናዎችን በመቋቋም ከፍተኛ ውጤት በማጣት ተሸላሚ በመሆኗ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማት ተናግራለች።

የኮሮና ወረርሽኝንና ሀገሪቱ ተከሰቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር በመቋቋም ከፍተኛ ወጣት በማምጣት ተሸላሚ በመሆኑ ከፍተኛ ደሰታ እንተሰማው የገለጸው ደግሞ ሌለው ተሸላሚ ተማሪ ቻለቻው መስፋን ነው።