በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚታዩ ማነቆዎችን ለማሻሻል እየሰራሁ ነው – – ባለስልጣኑ

1428

ጅማ፣ጥር 23/2013 (ኢዜአ) በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚታዩ ማነቆዎችን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን የፌደራል የኮንስትራክሽን ስራዎች ባለስልጣን ገለጸ፡፡

ባለስልጣኑ ‹‹ውጤታማ የኮንስትራክሽን ኢንድስትሪ ለኢትዮጵያ ብልጽግና›› በሚል መሪ ሀሳብ ከትላንት ጀምሮ በጅማ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ ከኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከጋምቤላ ክልሎች የተውጣጡ የዘርፉ የስራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

የባለስልጣኑ ከፍተኛ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ነገዎ እንደገለጹት ዘርፉ የተለያየ ፍላጎት ያለቸው ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት በመሆኑ በርካታ ፈታኝ ችግሮች አሉበት፡፡

የምክክር መድረኩ  ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ለይቶ ለመፍታት የሚያስቸሉ ግብአቶችን ለመሰብሰብና ግንዛቤ ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል የኮንስትራሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የህንጻ ግንባታ ቁጥጥርና አጽዳቂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጂነር አለሙ ሳሳባ በበኩላቸው ዘርፉ ለሀገር እድገት ወሳኝ ሚና እንዳለው  ተናግረዋል፡፡

የተቀናጀ አሰራር አለመኖሩና የስነ-ምግብር ችግሮች ለዘርፉ ማነቆዎች እንደሆኑ ጠቁማዋል፡፡

“በዘርፉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱ ተገቢ ነው” ብለዋል፡፡

ከጋንቤላ ክልል የመጡት አቶ ኩዋንግ ኦካያ “በዘርፉ ብዙ ጊዜ የአቅም ውስንነት ያለባቸው ድርጅቶች ፕሮጀክቶችን ወስደው እንደሚያጓትቱና አልፎም ገንዘብ ተቀብለው እንደሚጠፉ አመልክተዋል።

“ዘርፉ የመንግስት ሀብት የሚዘረፍበት ሆኗል” ያሉት አቶ ኩዋንግ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት  እንዳለበት አስገንዘበዋል፡፡

“ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ ህንጻዎችና መንገዶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መስራት አለባቸው” ሲሉም  አቶ ኩዋንግ አመልክተዋል፡፡