በፓርኩ በቱሪዝም መስክ የስራ ዕድል በመፍጠር የተደቀነበትን የመጥፋት አደጋ ለመከላከል ይሰራል–ኮሚሽኑ

1494

አርባምንጭ ጥር 23/2013 (ኢዜአ) በነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ በቱሪዝም መስክ የስራ ዕድል በመፍጠር በፓርኩ ላይ የተደቀነውን የመጥፋት አደጋ ለመከላከል አንደሚሰራ የፌዴራል የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አስታወቀ።

በፓርኩ በሚካሄድ የስራ ዕድል ፈጠራ የተለያዩ አማራጮችን በመፍጠርና በማስተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የሀይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ገልጿል።

የፌደራል የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን በወቅቱ ለኢዜአ እንደገለጹት በፓርኩ በማገዶ እንጨት ለቀማ፣ በህገወጥ ሰፈራና በከሰል ምርት ላይ የተሰማሩን በማደራጀት የስራ ዕድል ለመፍጠር ይሰራል።

በፓርኩ በርካታ ሰዎች ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያስችሉ አማራጮች እንዳሉ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ያሉት የስራ እድል አማራጮች ፓርኩን ከመጥፋት ስጋት የሚታደጉና ህብረተሰቡና ተፈጥሮ ተጣጥመው እንዲኖሩ ማድረግ የሚያስቸሉ ናቸው” ብለዋል።

የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክና የአርባዎቹ ምንጮች መገኛ የሆኑ ስፍራዎችን ተዘዋውረው እንደጎበኙ ገልጸው ያለፈው ትውልድ ያስረከበውን ያልተነካ ተፈጥሮ ለማስቀጠልና ፓርኩን ከጥፋት ለመከላከል የሚያስችል አማራጭ እንዳለ ከጉብኝቱ መረዳታቸውን አስታውቀዋል።

የሀይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን መስራች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ቀደም ሲል በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው አካባቢውን በደንብ ያውቁት እንደነበርና አሁን ላይ ደኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የመጣበት ሁኔታ እንዳለ አስታውሰዋል።

አካባቢውን ለመጠበቅ በደኑ ውስጥ እንጨት በመሰብሰብ የሚተዳደሩ እናቶችና ልጃገረዶችን አማራጭ አንዲፈጠርላቸው በማድረግ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

በፓርኩ የስራ እድል በመፍጠር በውስጡ የሚገኙ እንስሳትን ለመታደግ የሀይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን የማስተባበር ሀላፊነቱን ወስዶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

“አሁን ላይ በፓርኩ በተሰማራሁበት ስራ በወር 2 ሺህ ብር ደመወዝ እየተከፈለኝ ነው፤ ስራው ከዚህ ቀደም በጨለማ እንጨት ለመልቀም አደርገው የነበረውን ጉዞና ድካም አስቀርቶልኛል” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰላምነሽ ገና ናቸው።

ከዚህ ቀደም በፓርኩ ውስጥ እንጨት በመልቀም ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድሩ እንደነበርና አሁን ላይ በሀር ምርት የስራ እድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ወይዘሮ ሰላምነሽ ተናግረዋል።

በማህበር ተደራጅተው በተሰጣቸው ስልጠና በመታገዝ  በሀርትል ማራባትና ምርት ተሰማርተው የሚያገኙት ገቢ አነስተኛ ቢሆንም ነገ የተሻለ እንደሚሆንላቸው ተስፋ ሰንቀው በስራቸው እየተጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።